ልናቀው የሚገባ ከሁሉ የበለጠ ታሪክ

Bible and Candle

በመጀመሪያ አለማችን ባዶ ነበረች፡፡

አሶች በባህር፣

ከዋክብት በሰማይ ላይ አልነበሩም፤

ባህርና ውብ አበቦች የሉም ነበር፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔር ነበር፡፡

እግዚአብሔር አስደናቂ እቅድ ነበረው፡፡ ውብ የሆነች አለምን ለመስራት አሰበ፡፡ እንዳሰበም ፈጠራት፡፡ እግዚአብሔር አለምን ሲፈጥር ከምንም ነው የሰራት፡፡ “…..ይሁን” አለ፤ ሆነም!

ብርሀንን ፈጠረ፡፡ ወንዞችንና ባህርን፣ በሳር የተሸፈነች ምድርን፣ እንስሳትን፣ አእዋፋትንና ዛፎችን ሁሉ ሰራ፡፡

በመጨረሻ ሰውን ፈጠረ፡፡ ለፈጠረው ሰውም ሚስትን አበጀለት፡፡ ስማቸውም አዳምና ሔዋን ይባል ነበር፡፡

እግዚአብሐር አዳምና ሔዋንን በጣም ይወዳቸው ነበር፡፡ ይኖሩበት በነበረበት በውቡ ገነት ሁልግዜ አመሻሹ ላይ እየመጣ ያነጋግራቸው ነበር፡፡

አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር ከከለከላቸው ከአንድ ዛፍ በስተቀር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዲበሉ ተፈቅዶላቸው ነበር፡፡

አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔር ጠላት የሆነው ሰይጣን እስከፈተናቸው ቀን ድረስ በደስታ በገነት ይኖሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን እግዚአብሔር እንዳይበሉ ከከለከላቸው ዛፍ ፍሬ ለመብላት ወሰኑ፡፡ በዚህም ኃጢአትን ሰሩ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀፍረትና ሀዘን ገባቸው፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር እንደ ቀድሞው መነጋገር አልቻሉም፡፡ ያንን ፍሬ ከበሉ በኋላ መከራና ችግር ሊደርስባቸውና ሞትን ሊሞቱ ሆነ፡፡ በሰሩት ስህተት እንዴት ያለ ሀዘንን አዝነው ይሆን!

እግዚአብሔር ሊረዳቸው ቃል ገባላቸው፡፡ የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ልጁን ኢየሱስን ወደ አለም እንደሚልክና ኢየሱስም ከሰማይ ወርዶ ኃጢአት ይቅር እንዲባል መንገድን እንደሚያበጅ ነበር ተስፋን የሰጠው፡፡ የኃጢአት ይቅርታ እንዲሆን ኢየሱስ ለሰው ሁሉ መከራን መቀበልና መሞት ነበረበት፡፡ አዳምና ሔዋን እግዚአብሔር አዳኝን እንደሚልክላቸው ሲያውቁ እንዴት ያለ ታላቅ ደስታ ተሰምቷቸው ይሆን!

አዳምና ሔዋን ልጆችንና የልጅ ልጆችን ወለዱ፡፡ ቀስ በቀስም ብዙ ሰዎች በዚች ምድር ላይ መኖር ጀመሩ፡፡

እግዚአብሔር ሁሉ ሰው ደስተኛ እንዲሆን ይፈልግ ነበር፡፡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ነገራቸው፡፡ እግዚአብሔር እንዲያደርጉት የሰጣቸው ህግጋት ዝርዝር የሚከተለው ነው፡-

 1. ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡
 2. የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፡፡
 3. የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡
 4. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ፡፡
 5. አባትህንና እናትህን አክብር፡፡
 6. አትግደል፡፡
 7. አታመንዝር፡፡
 8. አትስረቅ፡፡
 9. በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር፡፡
 10. የባልንጀራህን ቤት አትመኝ የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ፡፡ (ዘጸአት 20፥3-17)

እነዚህን ህግጋት እኛም ማንበብ እንድንችል በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፈውልናል፡፡ ከታዘዝናቸውና ካደረግናቸው ደስተኞች እንሆናለን፡፡

ሰይጣን እነዚህን ህግጋት እንድንታዘዝ አይፈልግም፡፡ አንዳንዴ፣ በተለይም ደግሞ ሰው በማያየን ቦታ እንድንሰርቅ ይነግረናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁሉን የሚያይ አምላክ ስለሆነ የምናደረገውን ሁሉ ያውቃል፡፡

ሰይጣን አንዳንድ ግዜ ውሸትን እንድንዋሽና የዋሸነውን ውሸት ማንም እንደማያውቅብን እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁሉን የሚሰማ አምላክ ስለሆነ የምንለውን ሁሉ ያውቃል፡፡

አንዲህ ያሉ ኃጢአት ስንሰራ ውስጣችንን ሰላም አይሰማንም፡፡ እግዚአብሔር ስለሚወደን መልካም ሰዎች እንድንሆን ሊረዳን ይፈልጋል፡፡ ኢየሱስን ወደ አለም የላከውም ለዚህ ነው፡፡ የገባውን ተስፋ ፈጽሞ አልረሳም፡፡

ከብዙ አመታት በኋላ ኢየሱስ እንደ ሕጻን ተወለደ፡፡ አድጎም ሙሉ ሰው ሆነ፡፡

ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አደረገ፡፡ ሕሙማን ፈወሰ፣ እውራንን አበራ፣ ሕጻናትን ባረከ፡፡

ኢየሱስ ምንም በደል አልሰራም ነበር፡፡ ይልቁንም ለሰዎች ስለ እግዚአብሔርና እንዴት ሊታዘዙት እንደሚገባ አስተማራቸው፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ የኢየሱስ ጠላቶች ኢየሱስን በመስቀል ሰቅለው ገደሉት፡፡

ኢየሱስ መከራን ተቀብሎ የሞተው ለሰው ልጆች ሁሉ ኃጢአት ሲሆን፤ ይህ መስዋዕቱ የሰቀሉትንም ሰዎች ኃጢአት ያካትት ነበር፡፡

ኢየሱስ ከሞቱ በኋላ ተቀበረ፡፡ ነገር ግን ከዛን በኋላ አስደናቂ ነገር ሆነ፡፡ ኢየሱስ እንደተቀበረ አልቀረም፤ ከሙታን ተነሳ፡፡

ከትንሳኤው ጥቂት ጊዜ በኋላ እግዚአብሔር ኢየሱስን በደመና ወደ ሰማይ ወሰደው፡፡ መላዕክት ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ቆመው ሲመለከቱ ለነበሩ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሶ እንደሚመጣ ነገሯቸው፡፡

ኢየሱስ የሞተው ለእኛም ኃጢአት ጭምር ነው፡፡ ኃጢአታችንን ተጸጽተን እንድንናዘዝና ንስሀ እንድነገባ ይፈልጋል፡፡ ይህንን ብናደርግ ይቅርታን ሊሰጠን ዝግጁ ነው፡፡

በማንኛውም ግዜ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ትችላለህ፡፡ እርሱ እያንዳንዷን ቃላችንን የሚሰማና ሀሳባችንን ሁሉ የሚያውቅ አምላክ ነው፡፡ ኃጢአታችን ይቅር ሲባልልን በውስጣችን ደስታ እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ ከዛም መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድግ የምንፈልግ ሰዎች እንሆናለን፡፡

እግዚአብሔርን አለመታዘዝና ሰይጣንን መከተል እንመርጥ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል በዚህ ዓለም በምኖርበት ጊዜ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሻችን እምቢታ ከሆነ ወደ ገሀነም እንደምንጣል ይነግረናል፡፡ ገሀነም ለዘላለም ሲነድ የሚኖር እሳት ነው፡፡

ነገር ግን ኢየሱስን ብንወደውና ብንታዘዘው ወደ ምድር መጥቶ በሚመለስበት ጊዜ ወደ ሰማይ ይዞን ይሄዳል፡፡ መንግስተ ሰማይ የእግዚአብሔርና የልጁ የኢየሱስ ውብ መኖሪያ ነው፡፡ የፍቅርና የብርሀን ቤት ነው፡፡ በእዚያ ለዘላለም በደስታ እንኖራለን፡፡

ምን ያህል ታማኝ ነህ?

“እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ” (መዝሙር 51፡6)

ታማኝነት የእውነተኛ ህይወት መገለጫ ባህርይ ነው፡፡ ታማኝነት በዋናነት የልብ ጉዳይ ነው፡፡ ታማኝነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሰረታዊ መመሪያዎች አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር የልብን ሀሳብና መሻት ያውቃል፡፡ እውነተኝነት ለእግዚአብሔር መሰረታዊ መርህ ነው ምክንያቱም እርሱ የእውነት አምላክ ነው (ዘዳግም 32፡4)፡፡ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሆነ ልባችንን በእርግጥም ይባርካል፡፡

የሚታወቅብህ ከመሰለህ እውነትን፤ ማንም ማያውቅብህ ከሆነ ግን ውሸትን ትናገራለህን?

ሆን ብለህ ሰዎችን ወደ ተሳሳተ አመለካከት ትመራቸዋለህ?

መክፈል እንደማትችል እያወቅህ እዳ ውስጥ ትገባለህ?

ስትፀልይ ያለህበትን ሁኔታ በግልጽ ለእግዚአብሔር ትናገራለህ?

እግዚአብሔር እንድታደርግ ያሳወቀህን ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ?

ለመጽሀፍ ቅዱስ አትተምሮዎች ታማኝ ነህ?

በሰዎች ፊት ሆነህ እንደምትቀርበው ዓይነት ሰው ነህን?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሐናንያ እና ሰጲራ ስለሚባሉ ባልና ሚስት የተጻፈ አስደናቂ ታሪክ አለ (ሐዋ. ስራ 5፡1-11)፡፡ ሌሎች  ብዙዎች ያደርጉ እንደነበረው እነርሱም መሬታቸውን ሸጡ፤ ከሚስቱም ጋር ከሽያጩ እኩሌታውን ለማስቀረት በስውር ተስማምተው ሳለ ሙሉ ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ አስመሰሉ። ሐናንያና ሰጲራ መሬታችንን ይህን በሚያህል ዋጋ ሸጥነው በማለት ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች አመጡ፡፡ ለማታለል በመሞከራቸው እግዚአብሔር ወዲያውኑ በሞት ቀጣቸው፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሆነው በዚህ ክስተት ላይ ግብዝነት ወይም አለመታመን ለጥብቅ ቅጣት ሲያጋለጥ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ሀሰተኝነት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ እኛም እንደ ሐናንያና ሰጲራ ሰዎች ስለኛ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ልናደርግ እንችላለን፡፡ ለድርጊቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ እንደምንሆን እንዘነጋለን፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ስለሚያውቅ ፍጹም ታማኝነትን ከኛ ይፈልጋል፡፡

ግብዝ የሆነ ሰው ያልሆነውን እንደሆነ ያስመስላል፡፡ እውነተኛ ነኝ ይላል ነገር ግን ለጥቅሙ ሲሆን እውነታን ከማጋነን ወደ ኋላ አይልም፡፡ ችግረኞችን ስለመርዳት ያወራ ይሆናል ነገር ግን አደጋዎች ሲከሰቱ ጊዜና ገንዘቡን ለመለገስ ፈቃደኛ ይይደለም፡፡  አንድ ሰው የባልንጀራው ሁኔታ ከልቡ እንዳሳዘነው ሊያስመስል ይችላል ነገር ግን በችግር ወስጥ ያለ ባልነጀራውን ከመርዳት ይልቅ ማማት ይቀለው ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ታማኝ መስሎ ሊቀርብ ይችላል ነገር ግን እስካልታወቀበት ድረስ የሌላውን ሰው ገንዘብ ለመውሰድ ወደ ኋላ የማይል ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ አታላይም ሆኖ ሳለ በአስተሳሰቡ ብልጠት ከብዙ ሰዎች እንደሚሻል አድርጎ ራሱን ለማሳመን የሚጥር ይሆናል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች በአንዱ የተገኘ ሰው ታማኝ እንዳይደለ ወይም ግብዝ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሰዎች ግብዝ ባህርይ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ያሳዝናል፡፡ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” (ማቴዎስ 15፡8)፡፡ ለሰው በአፉ የሚናገረውንና በልቡ ያለውን ማስታረቅ ከባድ ነው፡፡ ከውስጥ ማንነታችን የሆነ ታማኝነት በጌታ ፊት ተቀባይነትን እና ፀጋን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡

እውነተኛ ክርስቲያን የታማኝነት ምሳሌ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ባለው ታማኝነት መጠን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያድጋል፡፡ አጠገባችን ካሉ ሰዎች ጋር ባለንም ግንኙነት ታማኝነት ጥንቃቄና አትኩሮት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ በቃላችንም ሆነ ተግባራችን አንዳችን በሌላችን ላይ እምነት የሚጣልብን ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ስለ እውነት የሚጠበቅብንን መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች ልንሆን ያስፈልገናል፡፡

ከሚቀጥለው ታሪክ ልንማር የምንችለው ትምህርት አለ፡፡ አንድ መምህር አንድን ልጅ እንዲህ ብላ ጠየቀችው “ለአንድ ብር ብለህ ውሸትን ትናገራለህ ?”

“አልናገርም መምህር” ሲል መለሰ ትንሹ ልጅ፡፡

“ለአምስት ብርስ ብለህ ውሸት ትናገራለህ?”

“አልዋሽም” አለ ልጁ፡፡

“ለአስር ብር ብለህ ውሸት ትናገራለህ”

“አልዋሽም” ነበር መልሱ፡፡

“ለአንድ ሺህ ብር ብለህስ ውሸት ትናገራለህ?

“ወይኔ” አለ በውስጡ “በአንድ ሺህ ብር ማድረግ የማልችለው ምን አለ?”

በማመንታት ላይ ሳለ ከኋላው የነበረ አንድ ሌላ ልጅ “አላደርገውም” አለ፡፡

“ለምን?” ጠየቀች መምህሯ፡፡

“ምክንያቱም ውሸት ይጣበቃል፤ አንድ ሺህ ብሩ ሲያልቅ፣ ከብሩ የሚገኘው ጥሩ ነገር ሁሉ ሲቆም ውሸቱ ግን እዛው እንደተጣበቀ ይቀራል”

እውነት ምቾት ቢነሳንም እንኳን ልንጠብቀው ፈቃደኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ከጊዜያዊ ሀፍረት ራሳችንን ለማዳን ብለን መዋሸት ሀቀኝነታችንን አሳልፈን በመስጠት የምንከፍለው ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ እምነትን በማጉደል የሚገኝ ገንዘብ ለቆሸሸ ህሊና እና በዚህ አይነቱ ኃጢአት ላይ እግዚአብሔር ለሚያኖረው ዘላለማዊ ፍርድ የሚከፈል ትንሽ ዋጋ ነው፡፡ 

ከታች የተዘረዘሩት ዓይነት ክፉ ስራዎች እየሰራህ በእግዚአብሔር ብርሀን እመላለሳለሁ ትላለህን?

 • ወንድም እና እህቶችህን ይቅር አለማለት
 • ሰዎችን አሳዝነህ ጥፋትህን አለማረም
 • እውነትን ማጋነን
 • ቃልህን አለመጠበቅ
 • የእግዚአብሔርን መባ እና አስራት መስረቅ

ታማኝነት የባህርይ መመዘኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ያውቃል፤ ከፊቱም የተሰወረ ምንም ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚያውቀን እና በውስጣችንም እንደሚሰማን ሆነን በእግዚአብሔር ፊት አንቀርብም፡፡ ታማኝነታችንን ወይም እውነተኛ ማንነታችንን  በሰዎች ፊት አንገልጠው ይሆናል፡፡ እውነተኛ ደስታ ያለው ሰው ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነና ትክክለኛ ማንነቱን የማይደብቅ ነው፡፡ ልባችንን ለእግዚአብሔር ግልጽ ስናደርግ እነዚህ ችግሮች መፍትሄን ያገኛሉ፡፡

አመለካከታችን እና መነሻ ሀሳባችን የታማኝነት ፈተናን ማለፍ አለባቸው፡፡ ይህንን ፈተና በእግዚአብሔር እና ሰዎች ፊት ለማለፍ ውስጣዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ውጫዊው ማንነታችን  የውስጣዊው ማንነታችን መገለጫ ነውና፡፡ ታማኝ ነህ? ታማኝነታችንን፤ እግዚአብሔር ይሻልዋል፣ ሌሎች ይጠብቁብናል፣ እኛም ተጠቃሚ እንሆንበታለን፡፡ የታማኝነት ህይወት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡ “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር” ወደናል (ዕብራውያን 13፡18)፡፡ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ” (ሮሜ 12፡17)፡፡  በተጨማሪ ዘሌዋውያን 19፡35-36 እና ምሳሌ 19፡5ን አንብብ፡፡

ሕይወትህ እነደ ተላከ ደብዳቤ ነው

የደብዳቤን ዋጋ የተረዳሁት ከአንድ አጎቴ በተላከልኝ፤ ነገር ግን በውስጡ ምንም ደብዳቤን ያልያዘ ፖስታ የደረሰኝ ዕለት ነው፡፡ ፖስታው ላይ አድራሻው በትክክል ተፅፎና ተገቢው ቴምብር ተለጥፎበት የነበረ ቢሆንም በፖስታው ውስጥ ግን ምንም አልነበረም፡፡  

ብዙዎቻችን በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች ደብዳቤዎች ይደርሱናል፡፡ ነገር ግን ከደብዳቤ የምንማረው መንፈሳዊ ትምህርት በጣም ጥቂት ነው፡፡  

ደብዳቤያችንን ወደ ፖስታ ቤት ይዘን ሄደን ወደ ምንፈልገው አድራሻ ከመላካችን በፊት ፖስታና ቴምብር (ወይም የመላኪያ ገንዘብ) ሊኖረን ይገባል፡፡   

እነዚህን ነገሮች ካሟላን በኋላ የተጻፈውን ደብዳቤ በፖስታ ውስጥ በመጨመር ተገቢውን ቴምብር እንለጥፍበታለን፡፡ የፖስታ ቤት ሰራተኞች በፖስታችን ላይ የለጠፍነው ቴምብር በሌላ ሰው ግልጋሎት ላይ እንዳይውል ማህተም ይመቱበታል፡፡ በስተመጨረሻም ለመላክ የተዘጋጀውን ፖስታ በመላኪያ ሳጥን ውስጥ እንከተዋለን፡፡

ማህተም ያረፈበት ፖስታ የተጻፈውን ደብዳቤ ይዞ ወደ ተላከበት ሰው አድራሻ ይሄዳል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈለት ሰው ደብዳቤው በደረሰው ጊዜ በደስታ ፓስታውን በመክፈት ለማንበብ ይጣደፋል፡፡ አንባቢው ፖስታውን በመቅደድ ወይም በጥንቃቄ በመክፈት ደብዳቤውን ካወጣ በኋላ ፖስታውን ከነቴምብሩ ጨመዳዶ ወደ ቆሻሻ መጣያ ይጥለዋል፡፡ በዚህም የፖስታውና የቴምብሩ ጉዞ ያበቃል፡፡ ደብዳቤውን ግን በጥሞና ለማንበብ አመቺ ጊዜንና ስፍራን ፈልጎ ይቀመጣል፡፡

እኛም ልክ እንደ ተላከ ደብዳቤ ነን፡፡ በእግዚአብሔር፤ ፖስታ በሆነ ስጋችን ውስጥ ተደርገን ወደ አለም የተላክን ደብዳቤዎች ነን፡፡ እኛ ግን የራሳችንን ማስጌጫ የሆነ ማህተም በመጨማመር ለስጋችን ያልተገባ ስፍራን እንሰጣለን፡፡ ጨምረንም የዚህችን አለም የኢኮኖሚና የትምህርት ስኬት እና ያልተገቡ ባህላዊ ግንኙነቶችን በመጨማመር በብዙም ይሁን በጥቂቱ የማህበራዊ ስኬት ቴምብርን በስጋችን ላይ እለጥፋለን፡፡ በነዚህ ነገሮች በጣም ከመወሰዳችን ተነሳ ብቸኛና ታላቅ ዋጋ ያላትን ነብሳችንን እንዘነጋለን፡፡

በመጨረሻም ተቀባያችን በሆነው ሞት እጅ እንወድቃለን፡፡ ሞትም ክብራችንንና ማዕረጋችንን ዋጋ አሳጥቶ የስጋችን ቆሻሻ መጣያ ወደ ሆነው መቃብራችን ይጥለናል፡፡ ሞት በአደጋ፤ በበሽታ ወይም በሌላ መንገድ ደብዳቤ የሆነችው ነብሳችንን በማውጣት የደብዳቤው ባለቤት ለሆነው ለሁሉ ቻይ አምላክ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ይህ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችንም በነብሳችን ምን መልእክት እንደተጻፈ ያነበናል፡፡

አንተ ሕይወትህን ስትመለከተው ባዶ መሆኑ አይታወቅህ ይሆናል፡፡ ሕይወትህ ባዶ እንዳትሆን በተለያዩ ተስፋ ሰጪ ተግባሮች ላይ ተሰማርተህ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የወዳጅህን መንፈሳዊ ግብዣ “በስራ ተጠምጃለሁ” በሚል ምክንያት ሳትቀበል ቀርተህ ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ስትታይ ግን ስራ ፈት ነህ፡፡  

በመጨረሻ በዘላለም አምላክ ፊት ቀርበህ “የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ምን አደረከው?” የሚለውን ጥያቄ ስትጠየቅ ወደ አለም በመመለስ ያለፈ ሕይወትህን ለማስተካከል ብትመኝ እንኳን ቴምብር የተለጠፈበት ፖስታ ሌላ አገልግሎት የማይሰጥ ተብሎ መጣሉ ይታወስሀለ፡፡ በዳኛው ፊት ቀርበህ “በግራው ያሉትን……እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” (ማቴዎስ 25፥41) የሚለውን ድምጽ ሰምተህ ምህረትን ብትለምን እንኳ ሰዓቱ የረፈደ ይሆናል፡፡

ቀጣይ የምትሰማው ድምጽ “በሕይወት በነበርክበት ጊዜ ሕይወትህን በከንቱ ስላባከንካት፤ አሁንም ወደ ዘላለም እሳት ተጥለህ ለምንም የማትጠቅም ትሆናለህ” የሚለውን ይሆናል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነውን ጌታ ፊት ለፊት ባየኸው ጊዜ ምን ያህል ከንቱ ሕይወትን በምድር ላይ እንደኖርክ ትገነዘባለክ፡፡                           

ኦ ውድ አንባቢ ሆይ! እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት “……ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሐንስ 6፥37) ላለው ኢየሱስ ልብህን ለምን አትሰጥም? ደብዳቤ የሆነች ነብስህ በእጁ ከመግባትዋ በፊት ለምን የሕይወትህ ጌታና አዳኝ አድርገህ አትሾመውም? አስታውስ “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር (ልጁን) ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ.3፡17)፡፡ ፖስታ የሆነውን ስጋህን በጥንቃቄ ስታስጌጥ ኖረህ በሕይወትህ መጨረሻ ላይ የደብዳቤው ባለቤት ከሁሉ አብልጦ ዋጋ የሚሰጠው ደብዳቤ ለሆነች ነብስህ መሆኑን ስትለዳ ምን ይሆን ትርፍህ? “…..አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” (ዘፍጥረት 3፥19)፡፡

በፈረጠመ የሞት እጅ የሕይወት ዘመን ደብዳቤ የሆነችው ነብስህ ተነጥቃ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ከመገናኘትዋ በፊት ያለፈው ዘመንህን ከንቱነት ለኢየሱስ ተናዘህ የሕይወትህ ባለቤት አድርገህ ተቀበለው፡፡  

ይህን ታደርግ ይሆን? ቀጠሮ አትስጥ፤ ዛሬውኑ አድርገው፤ የመዳን ቀን ዛሬ ነውና፡፡ ምን ታውቃለህ የነገው ቀን በጌታ ፍርድ ወንበር ፊት የምትቆበት ቀን ሊሆን ይችላል፡፡