ምን ያህል ታማኝ ነህ?

“እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ” (መዝሙር 51፡6)

ታማኝነት የእውነተኛ ህይወት መገለጫ ባህርይ ነው፡፡ ታማኝነት በዋናነት የልብ ጉዳይ ነው፡፡ ታማኝነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሰረታዊ መመሪያዎች አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር የልብን ሀሳብና መሻት ያውቃል፡፡ እውነተኝነት ለእግዚአብሔር መሰረታዊ መርህ ነው ምክንያቱም እርሱ የእውነት አምላክ ነው (ዘዳግም 32፡4)፡፡ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሆነ ልባችንን በእርግጥም ይባርካል፡፡

የሚታወቅብህ ከመሰለህ እውነትን፤ ማንም ማያውቅብህ ከሆነ ግን ውሸትን ትናገራለህን?

ሆን ብለህ ሰዎችን ወደ ተሳሳተ አመለካከት ትመራቸዋለህ?

መክፈል እንደማትችል እያወቅህ እዳ ውስጥ ትገባለህ?

ስትፀልይ ያለህበትን ሁኔታ በግልጽ ለእግዚአብሔር ትናገራለህ?

እግዚአብሔር እንድታደርግ ያሳወቀህን ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ?

የተሟላ መልዕክት ክፍል ምን ያህል ታማኝ ነህ?

ለመጽሀፍ ቅዱስ አትተምሮዎች ታማኝ ነህ?

በሰዎች ፊት ሆነህ እንደምትቀርበው ዓይነት ሰው ነህን?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሐናንያ እና ሰጲራ ስለሚባሉ ባልና ሚስት የተጻፈ አስደናቂ ታሪክ አለ (ሐዋ. ስራ 5፡1-11)፡፡ ሌሎች  ብዙዎች ያደርጉ እንደነበረው እነርሱም መሬታቸውን ሸጡ፤ ከሚስቱም ጋር ከሽያጩ እኩሌታውን ለማስቀረት በስውር ተስማምተው ሳለ ሙሉ ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ አስመሰሉ። ሐናንያና ሰጲራ መሬታችንን ይህን በሚያህል ዋጋ ሸጥነው በማለት ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች አመጡ፡፡ ለማታለል በመሞከራቸው እግዚአብሔር ወዲያውኑ በሞት ቀጣቸው፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሆነው በዚህ ክስተት ላይ ግብዝነት ወይም አለመታመን ለጥብቅ ቅጣት ሲያጋለጥ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ሀሰተኝነት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ እኛም እንደ ሐናንያና ሰጲራ ሰዎች ስለኛ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ልናደርግ እንችላለን፡፡ ለድርጊቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ እንደምንሆን እንዘነጋለን፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ስለሚያውቅ ፍጹም ታማኝነትን ከኛ ይፈልጋል፡፡

ግብዝ የሆነ ሰው ያልሆነውን እንደሆነ ያስመስላል፡፡ እውነተኛ ነኝ ይላል ነገር ግን ለጥቅሙ ሲሆን እውነታን ከማጋነን ወደ ኋላ አይልም፡፡ ችግረኞችን ስለመርዳት ያወራ ይሆናል ነገር ግን አደጋዎች ሲከሰቱ ጊዜና ገንዘቡን ለመለገስ ፈቃደኛ ይይደለም፡፡  አንድ ሰው የባልንጀራው ሁኔታ ከልቡ እንዳሳዘነው ሊያስመስል ይችላል ነገር ግን በችግር ወስጥ ያለ ባልነጀራውን ከመርዳት ይልቅ ማማት ይቀለው ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ታማኝ መስሎ ሊቀርብ ይችላል ነገር ግን እስካልታወቀበት ድረስ የሌላውን ሰው ገንዘብ ለመውሰድ ወደ ኋላ የማይል ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ አታላይም ሆኖ ሳለ በአስተሳሰቡ ብልጠት ከብዙ ሰዎች እንደሚሻል አድርጎ ራሱን ለማሳመን የሚጥር ይሆናል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች በአንዱ የተገኘ ሰው ታማኝ እንዳይደለ ወይም ግብዝ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሰዎች ግብዝ ባህርይ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ያሳዝናል፡፡ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” (ማቴዎስ 15፡8)፡፡ ለሰው በአፉ የሚናገረውንና በልቡ ያለውን ማስታረቅ ከባድ ነው፡፡ ከውስጥ ማንነታችን የሆነ ታማኝነት በጌታ ፊት ተቀባይነትን እና ፀጋን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡

እውነተኛ ክርስቲያን የታማኝነት ምሳሌ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ባለው ታማኝነት መጠን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያድጋል፡፡ አጠገባችን ካሉ ሰዎች ጋር ባለንም ግንኙነት ታማኝነት ጥንቃቄና አትኩሮት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ በቃላችንም ሆነ ተግባራችን አንዳችን በሌላችን ላይ እምነት የሚጣልብን ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ስለ እውነት የሚጠበቅብንን መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች ልንሆን ያስፈልገናል፡፡

ከሚቀጥለው ታሪክ ልንማር የምንችለው ትምህርት አለ፡፡ አንድ መምህር አንድን ልጅ እንዲህ ብላ ጠየቀችው “ለአንድ ብር ብለህ ውሸትን ትናገራለህ ?”

“አልናገርም መምህር” ሲል መለሰ ትንሹ ልጅ፡፡

“ለአምስት ብርስ ብለህ ውሸት ትናገራለህ?”

“አልዋሽም” አለ ልጁ፡፡

“ለአስር ብር ብለህ ውሸት ትናገራለህ”

“አልዋሽም” ነበር መልሱ፡፡

“ለአንድ ሺህ ብር ብለህስ ውሸት ትናገራለህ?

“ወይኔ” አለ በውስጡ “በአንድ ሺህ ብር ማድረግ የማልችለው ምን አለ?”

በማመንታት ላይ ሳለ ከኋላው የነበረ አንድ ሌላ ልጅ “አላደርገውም” አለ፡፡

“ለምን?” ጠየቀች መምህሯ፡፡

“ምክንያቱም ውሸት ይጣበቃል፤ አንድ ሺህ ብሩ ሲያልቅ፣ ከብሩ የሚገኘው ጥሩ ነገር ሁሉ ሲቆም ውሸቱ ግን እዛው እንደተጣበቀ ይቀራል”

እውነት ምቾት ቢነሳንም እንኳን ልንጠብቀው ፈቃደኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ከጊዜያዊ ሀፍረት ራሳችንን ለማዳን ብለን መዋሸት ሀቀኝነታችንን አሳልፈን በመስጠት የምንከፍለው ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ እምነትን በማጉደል የሚገኝ ገንዘብ ለቆሸሸ ህሊና እና በዚህ አይነቱ ኃጢአት ላይ እግዚአብሔር ለሚያኖረው ዘላለማዊ ፍርድ የሚከፈል ትንሽ ዋጋ ነው፡፡ 

ከታች የተዘረዘሩት ዓይነት ክፉ ስራዎች እየሰራህ በእግዚአብሔር ብርሀን እመላለሳለሁ ትላለህን?

  • ወንድም እና እህቶችህን ይቅር አለማለት
  • ሰዎችን አሳዝነህ ጥፋትህን አለማረም
  • እውነትን ማጋነን
  • ቃልህን አለመጠበቅ
  • የእግዚአብሔርን መባ እና አስራት መስረቅ

ታማኝነት የባህርይ መመዘኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ያውቃል፤ ከፊቱም የተሰወረ ምንም ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚያውቀን እና በውስጣችንም እንደሚሰማን ሆነን በእግዚአብሔር ፊት አንቀርብም፡፡ ታማኝነታችንን ወይም እውነተኛ ማንነታችንን  በሰዎች ፊት አንገልጠው ይሆናል፡፡ እውነተኛ ደስታ ያለው ሰው ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነና ትክክለኛ ማንነቱን የማይደብቅ ነው፡፡ ልባችንን ለእግዚአብሔር ግልጽ ስናደርግ እነዚህ ችግሮች መፍትሄን ያገኛሉ፡፡

አመለካከታችን እና መነሻ ሀሳባችን የታማኝነት ፈተናን ማለፍ አለባቸው፡፡ ይህንን ፈተና በእግዚአብሔር እና ሰዎች ፊት ለማለፍ ውስጣዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ውጫዊው ማንነታችን  የውስጣዊው ማንነታችን መገለጫ ነውና፡፡ ታማኝ ነህ? ታማኝነታችንን፤ እግዚአብሔር ይሻልዋል፣ ሌሎች ይጠብቁብናል፣ እኛም ተጠቃሚ እንሆንበታለን፡፡ የታማኝነት ህይወት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡ “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር” ወደናል (ዕብራውያን 13፡18)፡፡ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ” (ሮሜ 12፡17)፡፡  በተጨማሪ ዘሌዋውያን 19፡35-36 እና ምሳሌ 19፡5ን አንብብ፡፡

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ