ለመዳናችን በግል ማስረገጫ
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ብዙ ጊዜ “በግል መዳናችንን ማስረገጥ እንችላለን ወይስ አንችልም?” ብለው ለሚጠይቁት ጥያቄ መልስ ይሰጠን ይሆን? አንድ ሰው ኃጢያቱ ይቅር እንደተባለለት ያውቅ ይሆን? ወይስ ለማወቅ የፍርድ ቀን እስኪመጣ መጠበቅ ይኖርበታል? ይህን ወሳኝ ጥያቄ ለመመለስ እስከዚያን ቀን መቆየቱ አለመታደልና በጣም አደገኛ ውሳኔ ነው፡፡
አዎን፤ የፈለገ ሰው ማወቅ ይችላል፡፡ ጌታም ስለመዳናችን እርግጠኛ እንድንሆን ይፈልጋል፡፡ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ. 11፥28) እያለ ጥሪውን እያቀረበልን ነው፡፡ በዮሐ.3፥16 “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን (ኃጢያተኛውን፤ ሁሉንም) እንዲሁ ወዶአልና” ሲል ይነግረናል፡፡ ሰው ሁሉ ከፍጥረቱ ኃጢያተኛ በመሆኑ የእግዚአብሔርን ፍቃድ ከማድረግ ጎድሏል፡፡
ሰው በዚህ ባልተለወጠ ሁኔታው አዳኝ ያስፈልገዋል፡፡ በኃጢያቱና በመተላለፉ የሞተ በመሆኑ ከጥፋቱ የሚያድነው አዳኝ ያስፈልገዋል፡፡ ቸር እና መሀሪ የሆነው የሰማይ አምላካችን ለአስደናቂ ጸጋው እራሳቸውን አሳልፈው ለሚሰጡ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድነትን አዘጋጅቶላቸዋል፡፡ ኢየሱስ ደሙን በማፍሰስና “የኃጢአታችን ማስተሰሪያ” (1ኛ ዮሐ. 2፥2) በመሆን በመስቀል ላይ ሞቶልናል፡፡ ኃጢአተኛ ሰው ከኃጢአቱ ሊነፃና ለኃጢአቱም ምህረት እንደሚያስፈልገው ሊሰማው ይገባል፡፡ ኃጢአተኛነቱም ተሰምቶት “አምላክ ሆይ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” (ሉቃስ 18፥13) እያለ ሊለምን ይገባዋል፡፡ ከኃጢአተኛነት አካሄዱ ተጸጽቶና በደለኛነቱን ተገንዝቦ አስቀድሞ ኃጢያቱን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ሲኖርበት በመቀጠልም የበደላቸውን ሰዎች ይቅርታ መጠየቅና ለበደሉት ሁሉ ይቅርታ በማድረግ ከሰው ጋር ሰላምን ማውረድ ይገባዋል፡፡ የዓለምን ኃጢአት የሚስወግደውን የእግዚአብሔርን በግ (ዮሐ. 1፥29) በእምነት ቢመለከት ኢየሱስ ኃጢአቱን ሁሉ ይቅር ይለዋል፡፡
እግዚአብሔር ለኃጢአታችን ይቅርታ ማድረጉን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻል፡፡ አንዳንዴ በቀላል አነጋገር “ኃጢአትህ ተሰረየችልህ” (ሉቃስ 5፥20) ይላል፡፡ ኃጢአታችን ይቅር ከተባለልን ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ይኖረናል፡፡ “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” (ሮሜ 5፥1)፡፡ (በሌሎች ሰዎች ውሳኔ ስለተረጋገጠልን ወይም ስለተጠመቅን ወይም የቤተክርስቲያን አባል ስለሆንን ዳግመኛ ለመወለዳችን ማረጋገጫ ሊሆነን አይችልም፡፡) “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር እልፎአል፤ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” (2ኛ ቆሮ. 5፥17)፡፡ ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ በዮሐንስ ሶስት ላይ “እውነት እውነት እልሀለው፤ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ብሎ እንደነገረው በክርስቶስ የሆነ ሰው ሁሉ አዲስ ሆኖ ዳግም ተወልዷል፤ በመንፈስ መወለድ ማለትም እንዲህ ነው፡፡ የተፈጥሮ ልደት የተፈጥሮን ሕይወት ይሰጠናል፤ መንፈሳዊ ልደት ደግሞ መንፈሳዊ ሕይወትን ይሰጠናል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ሊመጣ የሚችለው ሰው “ከውኃ (ከእግዚአብሔር ቃል) እና ከመንፈስ ሲወለድ ነው (ዮሐ. 3፥5)፡፡
ከመንፈስ የተወለደ ሰው ከሞት (መንፈሳዊ ሞት) ትንሳኤን በማግኘት “በላይ ያለውን የሚሻ” (ቈላ. 3፡1) ነው፡፡ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞን ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” (ዮሐ. 5፥24) ፡፡
የተሟላ መልዕክት ክፍል ለመዳናችን በግል ማስረገጫ
በስጋቸው ሀሳብ ሳይሆን በመንፈስ ለሚመሩና “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፡1)፡፡ እንዲህ አይነቶቹ ሰዎች ፍቅራቸው ያተኮረው በላይ ባለው እንጂ በምድራዊው ነገር አይደለም፤ በምድር ያሉ ብልቶቻቸውን የሚገድሉና በስጋ ሀሳብና ፈቃድ የማይመላለሱ ናቸው፡፡ “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም” (1ኛ ዮሐ. 2፥15-16)፡፡ የእግዚአብሔር መንፈስ “የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ እራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል፡፡ ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፤ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች” (ሮሜ 8፥16-17) እንደሆንን ያስረግጥልናል፡፡
“በተሰጠንም በመንፈስ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን” (ሮሜ 5፥5) ሲፈስ፤ ያኔ ወደ ሰማያዊ ነገሮች እንዘረጋለን፡፡ ቃሉን በማፍቀርና ይህንን ቃል በመመገብ ስለ ጌታችን እንድንመሰክር ይሆንልናል፡፡
ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ ፍቅር ደግሞ ከተፈጥሯዊ ፍቅርና ከቤተሰባዊ ትስስር የበለጠ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ያለው ሁሉ ጠላቶቹን ይወዳል፤ የሚጠሉትንም እንዲያፈቅር ያስችለዋል (ማቴ. 5፡44)፡፡
ጌታ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱን ሲልካቸው “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. 28፥19-20) ብሎ አስተምሯቸዋል፡፡
የተለወጡና ዳግመኛ የተወለዱ ክርስቲያኖች በመንፈሱ ሕያው በሆነና ከእግዚአብሔር በተጠራ አገልጋይ የውሃ ጥምቀት ተጠምቀው የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ይቀላቀላሉ፡፡ ከዚያም ክርስትናው በጸሎት የተሞላ ሕይወት ይሆናል፡፡ ጸሎት ለክርስቲያን አስፈላጊ እስትንፋሱ ነው፡፡ “በጌታና በኃይኩ ችሎት” (ኤፌ. 6፥10) የበረታ እንዲሆን መንፈሳዊ አቅሙና እና ወኔው በጸሎት ይታደሳል፤ በዚህም “ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ” (ራእይ 3፡11) የሚለውን ለመተግበር ያስችለናል፡፡