ሕይወትህ እነደ ተላከ ደብዳቤ ነው
የደብዳቤን ዋጋ የተረዳሁት ከአንድ አጎቴ በተላከልኝ፤ ነገር ግን በውስጡ ምንም ደብዳቤን ያልያዘ ፖስታ የደረሰኝ ዕለት ነው፡፡ ፖስታው ላይ አድራሻው በትክክል ተፅፎና ተገቢው ቴምብር ተለጥፎበት የነበረ ቢሆንም በፖስታው ውስጥ ግን ምንም አልነበረም፡፡
ብዙዎቻችን በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች ደብዳቤዎች ይደርሱናል፡፡ ነገር ግን ከደብዳቤ የምንማረው መንፈሳዊ ትምህርት በጣም ጥቂት ነው፡፡
ደብዳቤያችንን ወደ ፖስታ ቤት ይዘን ሄደን ወደ ምንፈልገው አድራሻ ከመላካችን በፊት ፖስታና ቴምብር (ወይም የመላኪያ ገንዘብ) ሊኖረን ይገባል፡፡
እነዚህን ነገሮች ካሟላን በኋላ የተጻፈውን ደብዳቤ በፖስታ ውስጥ በመጨመር ተገቢውን ቴምብር እንለጥፍበታለን፡፡ የፖስታ ቤት ሰራተኞች በፖስታችን ላይ የለጠፍነው ቴምብር በሌላ ሰው ግልጋሎት ላይ እንዳይውል ማህተም ይመቱበታል፡፡ በስተመጨረሻም ለመላክ የተዘጋጀውን ፖስታ በመላኪያ ሳጥን ውስጥ እንከተዋለን፡፡
ማህተም ያረፈበት ፖስታ የተጻፈውን ደብዳቤ ይዞ ወደ ተላከበት ሰው አድራሻ ይሄዳል፡፡ ደብዳቤው የተጻፈለት ሰው ደብዳቤው በደረሰው ጊዜ በደስታ ፓስታውን በመክፈት ለማንበብ ይጣደፋል፡፡ አንባቢው ፖስታውን በመቅደድ ወይም በጥንቃቄ በመክፈት ደብዳቤውን ካወጣ በኋላ ፖስታውን ከነቴምብሩ ጨመዳዶ ወደ ቆሻሻ መጣያ ይጥለዋል፡፡ በዚህም የፖስታውና የቴምብሩ ጉዞ ያበቃል፡፡ ደብዳቤውን ግን በጥሞና ለማንበብ አመቺ ጊዜንና ስፍራን ፈልጎ ይቀመጣል፡፡
እኛም ልክ እንደ ተላከ ደብዳቤ ነን፡፡ በእግዚአብሔር፤ ፖስታ በሆነ ስጋችን ውስጥ ተደርገን ወደ አለም የተላክን ደብዳቤዎች ነን፡፡ እኛ ግን የራሳችንን ማስጌጫ የሆነ ማህተም በመጨማመር ለስጋችን ያልተገባ ስፍራን እንሰጣለን፡፡ ጨምረንም የዚህችን አለም የኢኮኖሚና የትምህርት ስኬት እና ያልተገቡ ባህላዊ ግንኙነቶችን በመጨማመር በብዙም ይሁን በጥቂቱ የማህበራዊ ስኬት ቴምብርን በስጋችን ላይ እለጥፋለን፡፡ በነዚህ ነገሮች በጣም ከመወሰዳችን ተነሳ ብቸኛና ታላቅ ዋጋ ያላትን ነብሳችንን እንዘነጋለን፡፡
በመጨረሻም ተቀባያችን በሆነው ሞት እጅ እንወድቃለን፡፡ ሞትም ክብራችንንና ማዕረጋችንን ዋጋ አሳጥቶ የስጋችን ቆሻሻ መጣያ ወደ ሆነው መቃብራችን ይጥለናል፡፡ ሞት በአደጋ፤ በበሽታ ወይም በሌላ መንገድ ደብዳቤ የሆነችው ነብሳችንን በማውጣት የደብዳቤው ባለቤት ለሆነው ለሁሉ ቻይ አምላክ አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ይህ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችንም በነብሳችን ምን መልእክት እንደተጻፈ ያነበናል፡፡
የተሟላ መልዕክት ክፍል ሕይወትህ እነደ ተላከ ደብዳቤ ነው
አንተ ሕይወትህን ስትመለከተው ባዶ መሆኑ አይታወቅህ ይሆናል፡፡ ሕይወትህ ባዶ እንዳትሆን በተለያዩ ተስፋ ሰጪ ተግባሮች ላይ ተሰማርተህ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የወዳጅህን መንፈሳዊ ግብዣ “በስራ ተጠምጃለሁ” በሚል ምክንያት ሳትቀበል ቀርተህ ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ስትታይ ግን ስራ ፈት ነህ፡፡
በመጨረሻ በዘላለም አምላክ ፊት ቀርበህ “የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ምን አደረከው?” የሚለውን ጥያቄ ስትጠየቅ ወደ አለም በመመለስ ያለፈ ሕይወትህን ለማስተካከል ብትመኝ እንኳን ቴምብር የተለጠፈበት ፖስታ ሌላ አገልግሎት የማይሰጥ ተብሎ መጣሉ ይታወስሀለ፡፡ በዳኛው ፊት ቀርበህ “በግራው ያሉትን……እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” (ማቴዎስ 25፥41) የሚለውን ድምጽ ሰምተህ ምህረትን ብትለምን እንኳ ሰዓቱ የረፈደ ይሆናል፡፡
ቀጣይ የምትሰማው ድምጽ “በሕይወት በነበርክበት ጊዜ ሕይወትህን በከንቱ ስላባከንካት፤ አሁንም ወደ ዘላለም እሳት ተጥለህ ለምንም የማትጠቅም ትሆናለህ” የሚለውን ይሆናል፡፡ ሁሉን ቻይ የሆነውን ጌታ ፊት ለፊት ባየኸው ጊዜ ምን ያህል ከንቱ ሕይወትን በምድር ላይ እንደኖርክ ትገነዘባለክ፡፡
ኦ ውድ አንባቢ ሆይ! እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት “……ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሐንስ 6፥37) ላለው ኢየሱስ ልብህን ለምን አትሰጥም? ደብዳቤ የሆነች ነብስህ በእጁ ከመግባትዋ በፊት ለምን የሕይወትህ ጌታና አዳኝ አድርገህ አትሾመውም? አስታውስ “ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር (ልጁን) ወደ ዓለም አልላከውም” (ዮሐ.3፡17)፡፡ ፖስታ የሆነውን ስጋህን በጥንቃቄ ስታስጌጥ ኖረህ በሕይወትህ መጨረሻ ላይ የደብዳቤው ባለቤት ከሁሉ አብልጦ ዋጋ የሚሰጠው ደብዳቤ ለሆነች ነብስህ መሆኑን ስትለዳ ምን ይሆን ትርፍህ? “…..አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” (ዘፍጥረት 3፥19)፡፡
በፈረጠመ የሞት እጅ የሕይወት ዘመን ደብዳቤ የሆነችው ነብስህ ተነጥቃ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ከመገናኘትዋ በፊት ያለፈው ዘመንህን ከንቱነት ለኢየሱስ ተናዘህ የሕይወትህ ባለቤት አድርገህ ተቀበለው፡፡
ይህን ታደርግ ይሆን? ቀጠሮ አትስጥ፤ ዛሬውኑ አድርገው፤ የመዳን ቀን ዛሬ ነውና፡፡ ምን ታውቃለህ የነገው ቀን በጌታ ፍርድ ወንበር ፊት የምትቆበት ቀን ሊሆን ይችላል፡፡