የጌታ የመምጫው ጊዜ ቀርቧል

ሌባ ሳይታሰብ በሌሊት እንደሚመጣ ጌታም እንዲሁ በድንገት ይመጣል (2ኛ ጴጥሮስ 3፡19)፡፡ የጌታ የመምጫ ጊዜ ቅርብ እንደሆነ ለምን እናምናለን? በዙሪያህ እየሆነ ያለውን ስትመለከት፤ ምን ያሳስብሀል?

መጽሀፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን ምን እንደሚሆን ይነግረናል፡፡ የተነገረውም እያንዳንዱ ነገር እየተፈፀመ ነው፡፡ “በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥ የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል” (ማቴዎስ 24፡38-39)፡፡ እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ዓለም ሰው ራስ ወዳድና የልቡም ሀሳብ ክፉ ስለነበረ በውሀ አጠፋው፡፡ ዓለም በአመፃ የተሞላች ነበረች፡፡ እነሱም “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ” (2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡4) ነበሩ፡፡ ዛሬም ሰዎች ከመቼውም ይልቅ ተድላን የሚወዱ ሆነዋል፤ ተድላን ለማግኘትም የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡

ዓለም ያለችበትን ሁኔታ እስኪ እንመልከት፡፡ ክፋት እና ጥላቻ በብዙ ከተሞች ላይ አይሏል፡፡ ደም መፋሰስና ግድያ እለታዊ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ ለምን? ሰዎች እግዚአብሔርን ረስተዋል፡፡ ወጣቶች ቀዥቃዦችና ያልተረጋጉ ሆነዋል? እናትና አባት ልጆቻቸው የቅርብ ክትትል በሚያስፈልጋቸው ወቅት ትተዋቸው ከቤት ርቀው ሄደው  ይሰራሉ፡፡ ወደ ጎዳኖች በመውጣት ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ በወጣትነት እድሜያቸው የሚቀጩ ሰዎች ቁጥር ከአመት አመት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ወንጀል ከቀላል ደረጃ ወደ አስከፊ ደረጃ ደርሶአል፡፡ ምን ታስባለህ፤ ነገሮች የሚሻሻሉ ይመስልሀል? ለውጥ የሚታይበት ነገር ተመልክተሀል? ይህ ሁኔታ እስከመቼ ይቀጥል ይሆን? እግዚአብሔር ታጋሽ ነው ነገርግን መንፈሱ ሁሌም ከሰው ጋር ሲታገል አይኖርም፡፡ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ስራቸው መልስ የሚሰጡበት የቁርጥ ቀን ይመጣል፡፡  

የዛሬ ጊዜ ክርስቲያንስ እንዴት ነው? ቅድሚያ መስጠት ላለበት ነገር ቅድሚያን የሚሰጥ ነው? ወይስ ዓለማዊ  ነገሮች አጨናግፈውት እውነተኛ ብርሃኑን እንዳያበራ አግደውታል? የምድር ጨው የማዳን ሀይሉን አጥቶ ይሆን? መጽሀፍ ቅዱስ በእናንተ ያለው ብርሃን ጨልሞ ከሆነ ጨለማው እንዴት ከፍቷል ይለናል፡፡ አዎን ሁላችንም ብርሃኑ እንደበዘዘ ማስተዋል እንዳለብን አምናለሁ፤ ነፍሳትም ሁሉ በታላቁ ፈራጅ ፊት ቆመው ስለ ስራቸው ምላሽ የሚሰጡበት ቀን ቅርብ ነው፡፡

መጽሀፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚለን ኢየሱስ ይመጣል፡፡ “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ደግሞም የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደስማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (የሐዋ. ስራ 1፡9-11)፡፡ ወዳጄ ሆይ፤ ይህ ክስተት ሲሆን አያመልጠንም፡፡ አይን ሁሉ ሲመጣ ያዩታል፡፡ ጌታ ይመጣል፤ ሲመጣም “አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል” (ማቴዎስ 25፡32)፡፡ የተወሰኑት ከእርሱ ጋር ወደ ክብር ይሄዳሉ ሌሎች ይቀራሉ፡፡ አንተስ አብረህ ወደ ክብር ትሄዳለህ ወይስ ወደ ኋላ ትቀራለህ? መምረጥ አለብህ፡፡

እኛ ሁላችን ሀጢአተኞች ነን

የተሟላ መልዕክት ክፍል የጌታ የመምጫው ጊዜ ቀርቧል

ሁላችንም ሀጢአትን የሚሰራ ተፈጥሮ አለን፤ ለሀጢአት ባሮች ነን፡፡ እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ተፍተናል፡፡ መልካም የሚያደርግ የለም አንድስ አንኳ፡፡ ማንም ከሀጢአት የነፃሁኝ ነኝ ሊል አይችልም፡፡ መዋሸት፣ ማታለልና መስረቅ የሰው ተፈጥሮው ነው፡፡ ከልጅነታችን ትክክል እንዳልሆኑ እያወቅን የምናደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ወደ አዋቂነት እድሜ መጥተንም እነዛኑ ነገሮች ለማድረግ እንደምንፈልግ አውቀናል፡፡ ሀጢአት ደመዎዝ አለው፡፡ ዋጋውን ሳይቀበል አይቀርም “በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና” (ገላትያ 6፡8)፡፡ ለሀጢአታችን ብዛት የሚገባውን ካሳ መክፈል የምንችልበት አቅም የለንም፤ ሀጢአትም ከቶ ወደ መንግስተ ሰማይ ሊገባ አይችልም፡፡ ስለዚህ ምን ይበጀናል? ንሰሀ ካልገባን  በስተቀር ተስፋ በሌለበት እንቀራለን፡፡  

አንድ ቀን ጌታ የተዘጋጁትን፣ ዳግም የተወለዱትን ከእርሱ ጋር በክብር እንዲሆኑ ሊወስዳቸው ከሰማይ ይወርዳል (1ኛ ተሰሎንቄ 4፡16-17)፡፡ መንግስተ ሰማይ ያማረና አስደሳች ይሆናል፡፡ “ነገር ግን። ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰውም ልብ ያልታሰበው እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው” (1ኛ ቆሮንጦስ 2፡9)፡፡ ዝግጁዎች ካልሆንን ወደ ኋላ እንቀራለን፡፡ መጽሀፍ ቅዱስ፣ ከዚያ በኋላ ምድር በታላቅ ትኩሳት ይቀልጣል ይላል፡፡ ይህም እሳት ለዘለአለም እንደሚሆን ይነግረናል “ትላቸው ወደማይሞትበት እሳቱም ወደማይጠፋበት” (ማርቆስ 9፡44)፡፡ በዚያ ለዘለአለም ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ይሆናል፡፡ ወደ ኋላ ለሚቀሩት ስቃይና መከራ ይሆንባቸውል፡፡ “የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል” (ራዕይ 14፡11) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ጠባብ አእምሮአችን ሊረደው አይችልም፡፡ የጠፋ፤ የተጣለ! ወደ ፊት የተሸለ ይሆናል የሚል ተስፈ የለም፡፡

ከሁሉ የሚያስከፋው፤ ከትዕቢት እና ከቸልተኝነት፣ ከተድላ ወዳጅነትና ከሀጢአት የተነሳ የዘላለም ህይወት ስጦታን ልናጣው መቻላችን ነው፡፡ ጥፋቱ የራሳችን እንጂ የማንም አይሆንም፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር  ከዘለአለም ሞት እጣ ፈንታ ሊያስመልጠን የደህንነትን መንገድ ስላዘጋጀልን ሁልጊዜ መዳን እንችል እንደነበረ አውቀን በምርጫችን በገሀነም እንሆናለን፡፡

ከ ዮሀንስ 3፡16-17 ስለ እግዚአብሔር ፍቅር የተሻለ ማብራሪያን ሊሰጥ የሚችል የለም፡፡ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና”፡፡ ኢየሱስ ሁሉንም ሰው ወደ ህይወት ይጠራል፤ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።  ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና”፡፡

በብሉይ ኪዳን ዘመን ሁሉ የነበሩ ሰዎች የኮርማ፣ የጠቦት፣ የፍየል እና የእርግብን ደም በማፍሰስ ለሀጢአት ስርየት እንዲሆንላቸው መስዕዋት ያቀርቡ ነበር፡፡ ለሀጢአት ስርይትን ለማግኘት ሞትና የደም መፍሰስ ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ተገንዝበው ነበር፡፡ ኢሳያስ 53 ስለ ኢየሱስ “ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፥ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም” ብሎ ይነግረናል፡፡ አዎን፤ ካለንበት ከጥፋት መንገድ ለመመለስ ኢየሱስን እንደ አዳኛችን አድርገን መቀበል አለብን፡፡ የእርሱ ደም ለኛ ሀጢአት ስርየት ሆነ፤ የሄደበትን መንገድ መከተል አለብን፡፡ “ኢየሱስም። እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሀንስ 14፡6)፡፡ “ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሀንስ 6፡37)፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኢየሱስ ይጠቁመናል፤ የዓለምን ሀጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ይለዋል፡፡ መጽሀፍ ቅዱስ ኢየሱስ በምድር ላይ እንዴት እንደኖረ፤ ሸክማቸው የከበደባቸውን እንዴት እንዳሳረፈ፣ የታመሙትን እንደፈወሰ እና ለሞቱት ህይወትን እንደ ሰጠ ይነግረናል፡፡ በመጨረሻም በመስቀል ላይ እንደሞተ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሳም ይነግረናል፡፡ እርሲ ፍጹም የደህንነት መንገድ ሆኖልናል፡፡ ታድያ ይህን ታላቅ የደህንነት መንገድ ቸል ብንል ከእግዚአብሔር ቁጣ እንዴት እናመልጣለን?

የክርስቲያን ሀላፊነት

ከጥቂት ጊዜ በኋላ በምድር ላይ ያለን ቆይታ ያበቃል፡፡ ዋናው ጥያቄ፣ ሀላፊነታችንን ተወጥተናል? ለጠፉ ነፍሳት ስለ ክርስቶስ የመመስከር እድሉን አግኝተን ሳናደርገው ስንቀር አጋጣሚው ያልፈናል፡፡ ያቺ ነፍስ ክርስቶስን ሳታውቅ ወደ ዘለአለም ከተሸገረች ግዴታችንን ተወጥተናል ማለት እንችላለን? ለግድ የለሽነታችን ምን ምላሽ እንሰጣለን?

ጌታ በነብዩ ሕዝቅኤል በኩል እንዲህ ይናገራል፤ “እኔ ኃጢአተኛውንበእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ” (ሕዝቅኤል 3፡18)፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ ያሉትን አራት ተከታታይ ጥቅሶች አንብብ፡፡ እንነዚህ ጥቅሶች ሊያስፈሩንና ያለብንን ትልቅ ሀላፊነት ሊያስገነዝቡን ይገባል፡፡ እኛ ምስክሮቹ ነን፡፡ ለምድራዊ ነገሮች ያለን አመለካከትና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለን ትጋት ሰዎች ስለ ክርስትና በሚኖራቸው አመለካከት ላይ ተጽኖ ያሳድራል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ሀይል ልንሞላ ያስፈልገናል፡፡ ልባችንም በእግዚአብሔር ፍቅር መሞላት አለበት፡፡ እውነተኛ ምስክሮች እንድንሆን ለሚመፉ ነፍሳት ግድ ሊለን ይገባል፡፡ ብዙ ጊዜ ልባችን እንዲነሳሳ ተግተን ከመጸለይ ይልቅ ይህ እስኪሆን ዝም ብለን እንጠብቃለን፡፡ ክርስቲያን ሆይ ዛሬ፤ በፊታችን ላለው ትግል እራሳችንን እንዴት እናበረታታው? ሀላፊነታችንን እንወጣ ይሆን ወይስ የዘላለም ህይወት ስጦታን እናጣዋለን፡፡ ለጌታ ማድረግ ያለብንን አሁን እናድርግ! “ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም” (እብራውያን 10፡37)፡፡

ጌታ ሊመጣ ነው፣ ጊዜው መች እንዲሆን ባናውቅም
በእኩለ ሌሊት አሊያም በጠዋት በቀትርም
ምሽትም ላይ ቢሆን፣ ይመጣል ሊወስደን
እንጠብቀው ይሆን፣ ሁሌም ተዘጋጅተን?

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ