ንስሐ የምህረት በር

የሰው ልጅ ቅዱስ በሆነው በእግዚአብሔር ፊት በኃጢአቱ ወንጀለኛ ሆኖ በመገኘቱ ሞት እንደተፈረደበት ታውቃለህ? ከዚህ የዘላለም ሞት ፍርድ አምልጦ ለዘላለም ይድን ዘንድ የእግዚአብሔርን ምህረት መቀበል አለበት፡፡ ከዘላለም ሞት አንፃር ምህረት ማለት እግዚአብሔር የሰው ልጅ ሊቀበል ለሚገባው ፍርድ ይቅርታን ሲያደርግ ነው፡፡ ምንም እንኳ ድነት ነጻ የማይከፈልበትና በስራችን የምናገኘው ባይሆንም እግዚአብሔር ግን ምህረቱን ለሰው ልጅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አይደለም የሰጠው፡፡ እግዚአብሔር ምህረት የሚደርግበት ቅድመ ሁኔታ ንስሐ ነው፡፡

መጥምቁ ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ቃል እየሰበከ ሲመጣ ግልጽና ጠንካራ የነበረው መልዕክቱ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴዎስ 3፥20) የሚል ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስም አገልግሎቱን የጀመረው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴዎስ 4፥17) በሚል ተመሳሳይ መልዕክት ነበር፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ በ(የሐዋርያት ስራ 3፥19) ላይ “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱም” እንዳለው ለመዳን ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው፡፡ የምህረት በር ተከፍቶ ድነት የሚገኘው በንስሐ አማካኝነት ነው፡፡

ሁሉ ኃጢአትን ሰርተዋል

በዓለማችን ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ ሲኖር፤ በብዙ መንገዶች አንዳችን ከአንዳችን እንለያያለን፡፡ ነገር ግን “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፥23) የሚለውን መልዕክት ሁላችንም እንጋራዋለን፡፡ ጨምሮም “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ” (ሮሜ 3፥10) ይላል፡፡ እግዚአብሔር በነብዩ ኢሳይያስ ሲናገር “እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ” (ኢሳይያስ 53፥6) ይላል፡፡ የነዚህን ጥቅሶች ዋና ሐሳብ ልብ ብለሀል? “እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ”፤ “አንድም ጻድቅ የለም”፤ ““ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋል”፡፡ እነዚህ ጥቅሶች አንተን አያካትቱ ይሆን? ነብስህና ሕይወትህ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ወንድም ይሁን ሴት ማንም እግዚአብሔርን የሕይወቱ ጌታ አድርጎ የማይቀበል ሁሉ በአመጻና በኃጢአት ይኖራል፡፡ “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች” (ሕዝቅኤል 18፥4)፡፡

ኃጢአት ያለያያል

ኃጢአትህ ከእግዚአብሔር ጋር አለያይቶሀል፡፡ ልትገልጸው የማትችለው ናፍቆት በውስጥህ ይሰማሀል፡፡ የተረሳህና እግዚአብሔርም የማይሰማ ሊመስልህ ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ይህ ለምን እንደሆነ ምክንያቱን እንዲህ ሲል ይነግረናል፡- “እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል (ኢሳይያስ 59፥1-2)። ጨምሮም (ሮሜ 6፥23) ላይ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” ይለናል። ስለ ሕይወትህና ስለ ኃጢአትህ ስታስብ ስለ እግዚአብሔርም አስብ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ኃጢአት የለም፡፡ ስለዚህ እርሱ ቅዱስ ጻድቅና የማያዳላ አምላክ ነው፡፡ “እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ (በማምጣት)” (መክብብ 12፥14) ለኃጢአት ፍርድ እንደሚገባው ይነግረናል። በአንተና በእግዚአብሔር መካከል ሰፊ መራራቅ ተፈጥሯል፡፡ በቅዱሱ እግዚአብሔር እና በኃጢአተኛው ሰው መካከል የተፈጠረውን መራራቅ የሚያስታርቀውን መንገድ እስካላገኘህ ድረስ የዘላለም ሞትን ትሞታለህ! (ሉቃስ 16፥26)፡፡ ነገር ግን የምስራች፣ መንገድ አለ፣ ተስፋም አለልህ!

የተሟላ መልዕክት ክፍል ንስሐ የምህረት በር

እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የሞትን ፍርድ ያስተላለፈ ቢሆንም፤ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” (1ዮሐንስ 4፥16) እንደሚል እርሱ የፍቅር አምላክ ነው፡፡ በኃጢአት የምትኖር እንኳን ቢሆን እግዚአብሔር ይወድሀል፡፡ ከፍቅሩ የተነሳ ትድን ዘንድ መንገድን አዘጋጅቶልሀል (ዮሐንስ 3፥16)፡፡ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ የፈረደውን ፍርድ ቢፈጽም ሰው በቅጽበት ይሞታል፡፡ ነገር ግን ማንም እንዲይጠፋ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የኃጢአታችንን ቅጣት ተቀብሎልን በሕይወት እንኖር ዘንድ ልጁን ኢየሱስን ልኮልናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭከና ተመልከት” (ሮሜ 11፥22)  ይላል፡፡ የእግዚአንሔር ቸርነት ሰው ሁሉ እንዲድን መፈለጉ ሲሆን ፍርዱ ደግሞ መቀጣት ያለበትን ሁሉ ይቀጣል፡፡

ኢየሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ነብሳችንን ለማዳን ነው፡፡ እርሱ ምንም ኃጢአት ያልተገኘበት ቅዱስ የእግዚአብሔር በግ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለኛ ያለው ፍቅር የተረጋገጠው ኃጢአትና በደላችንን ሁሉ ወስዶ በኢየሱስ ላይ ባኖረበት ግዜ ነው፡፡ ቸርነቱን ተመልከት! ኢየሱስ በኛ ቦታ ሆኖ ኃጢአት በመሆን የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲፈጸም በመስቀል ላይ ተሰቀለ፡፡ መከራና ስቃይንም ተቀብሎ ሞተ፡፡ የኃጢአታችንም ዋጋ ተከፈለ፡፡ የእግዚአብሔርን ጭካኔ ተመልከት!

ንስሐ፣ የእኛ ድርሻ

ኢየሱስ እንደሞተልህ ትረዳ ይሆን? በኃጢትህ ምክንያት መሞቱንስ ታስተውል ይሆን? ኢየሱስን የሰቀለው ማን ነበር? የአይሁድ መሪዎች፣ ጲላጦስ ወይስ የሮም ወታደሮች ብቻ ይሆኑ ለኢየሱስ መሰቀል ተጠያቂዎች? ሐዋርያው ጴጥሮስ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሲሰብክ “……ሰቅላችሁ ገደላችሁት” በማለት ይሰሙት የነበሩት ህዝብ ለኢየሱስ መሰቀል ተጠያቂዎች እንደነበሩ በ(የሐዋርያት ስራ 2፥16) ላይ ሲነግራቸው እናነባለን፡፡ ተሰቅሎ ወደነበረው ኢየሱስ ተመልከትና ለኃጢአተኛነትህ እውቅናን ስጥ፡፡

የጠፋህ መሆንህና እርዳታ እንደሚያስፈልግህ በእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ትረዳለህ፡፡ ይህ መረዳት በልብህ እየጠነከረ ሲመጣ የኃጢአተኝነት ሸክም በርትቶ ስለ ኃጢአትህ መጸጸት እንዲሆንልህ ያደርጋል፡፡ ያን ጊዜም “እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ” (ሉቃስ 18፥13) በማለት ወደ እግዚአብሔር መጮህ ይሆንልሀል፡፡ እግዚአብሔርም ከልብ የሆነ ጩኸትህን ሰምቶ ያድንሀል፡፡ ሸክምህም ሁሉ ተራግፎልህ ዳግም ትወለዳለህ፡፡ ኢየሱስን መከተልህን ስትቀጥል ከኃጢአት መንገዶችህ ሁሉ ፊትህን በማዞር ሰማያዊውን መንገድ ትከተላለህ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ለሚመጡ ሁሉ በልባቸው የሚሰራው ስራ እና የንስሐ መንገድ ይህን ይመስላል፡፡ ልብህ ታጥቦና ነጽቶ ሰላም ደስታና መተማመን ይሆንልሀል፡፡

በመጨረሻም ንስሐ በክርስቶስንና በእግዚአብሔርን ፍቃድ ደስ እየተሰኘህ አመስጋኝና ታማኝ እንድትሆን ያደርግሀል፡፡ ሞት ተፈርዶብንና መውጫው ጠፍቶን ሳለ ክርስቶስ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፥28) አለን። “እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን” (1ዮሐንስ 4፥19)፡፡   

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ

ምን ያህል ታማኝ ነህ?

“እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፤ የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ” (መዝሙር 51፡6)

ታማኝነት የእውነተኛ ህይወት መገለጫ ባህርይ ነው፡፡ ታማኝነት በዋናነት የልብ ጉዳይ ነው፡፡ ታማኝነት ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሰረታዊ መመሪያዎች አንዱ ነው፡፡ እግዚአብሔር የልብን ሀሳብና መሻት ያውቃል፡፡ እውነተኝነት ለእግዚአብሔር መሰረታዊ መርህ ነው ምክንያቱም እርሱ የእውነት አምላክ ነው (ዘዳግም 32፡4)፡፡ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሆነ ልባችንን በእርግጥም ይባርካል፡፡

የሚታወቅብህ ከመሰለህ እውነትን፤ ማንም ማያውቅብህ ከሆነ ግን ውሸትን ትናገራለህን?

ሆን ብለህ ሰዎችን ወደ ተሳሳተ አመለካከት ትመራቸዋለህ?

መክፈል እንደማትችል እያወቅህ እዳ ውስጥ ትገባለህ?

ስትፀልይ ያለህበትን ሁኔታ በግልጽ ለእግዚአብሔር ትናገራለህ?

እግዚአብሔር እንድታደርግ ያሳወቀህን ሁሉ በታማኝነት ታደርጋለህ?

የተሟላ መልዕክት ክፍል ምን ያህል ታማኝ ነህ?

ለመጽሀፍ ቅዱስ አትተምሮዎች ታማኝ ነህ?

በሰዎች ፊት ሆነህ እንደምትቀርበው ዓይነት ሰው ነህን?

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሐናንያ እና ሰጲራ ስለሚባሉ ባልና ሚስት የተጻፈ አስደናቂ ታሪክ አለ (ሐዋ. ስራ 5፡1-11)፡፡ ሌሎች  ብዙዎች ያደርጉ እንደነበረው እነርሱም መሬታቸውን ሸጡ፤ ከሚስቱም ጋር ከሽያጩ እኩሌታውን ለማስቀረት በስውር ተስማምተው ሳለ ሙሉ ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ አስመሰሉ። ሐናንያና ሰጲራ መሬታችንን ይህን በሚያህል ዋጋ ሸጥነው በማለት ገንዘቡን ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች አመጡ፡፡ ለማታለል በመሞከራቸው እግዚአብሔር ወዲያውኑ በሞት ቀጣቸው፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በሆነው በዚህ ክስተት ላይ ግብዝነት ወይም አለመታመን ለጥብቅ ቅጣት ሲያጋለጥ እናያለን፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ሀሰተኝነት አጥብቆ ይቃወማል፡፡ እኛም እንደ ሐናንያና ሰጲራ ሰዎች ስለኛ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ልናደርግ እንችላለን፡፡ ለድርጊቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ እንደምንሆን እንዘነጋለን፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ስለሚያውቅ ፍጹም ታማኝነትን ከኛ ይፈልጋል፡፡

ግብዝ የሆነ ሰው ያልሆነውን እንደሆነ ያስመስላል፡፡ እውነተኛ ነኝ ይላል ነገር ግን ለጥቅሙ ሲሆን እውነታን ከማጋነን ወደ ኋላ አይልም፡፡ ችግረኞችን ስለመርዳት ያወራ ይሆናል ነገር ግን አደጋዎች ሲከሰቱ ጊዜና ገንዘቡን ለመለገስ ፈቃደኛ ይይደለም፡፡  አንድ ሰው የባልንጀራው ሁኔታ ከልቡ እንዳሳዘነው ሊያስመስል ይችላል ነገር ግን በችግር ወስጥ ያለ ባልነጀራውን ከመርዳት ይልቅ ማማት ይቀለው ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ታማኝ መስሎ ሊቀርብ ይችላል ነገር ግን እስካልታወቀበት ድረስ የሌላውን ሰው ገንዘብ ለመውሰድ ወደ ኋላ የማይል ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ አታላይም ሆኖ ሳለ በአስተሳሰቡ ብልጠት ከብዙ ሰዎች እንደሚሻል አድርጎ ራሱን ለማሳመን የሚጥር ይሆናል፡፡ ከነዚህ ሁኔታዎች በአንዱ የተገኘ ሰው ታማኝ እንዳይደለ ወይም ግብዝ መሆኑን ያሳያል፡፡

የሰዎች ግብዝ ባህርይ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ያሳዝናል፡፡ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው” (ማቴዎስ 15፡8)፡፡ ለሰው በአፉ የሚናገረውንና በልቡ ያለውን ማስታረቅ ከባድ ነው፡፡ ከውስጥ ማንነታችን የሆነ ታማኝነት በጌታ ፊት ተቀባይነትን እና ፀጋን ለማግኘት ቁልፍ ነው፡፡

እውነተኛ ክርስቲያን የታማኝነት ምሳሌ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ባለው ታማኝነት መጠን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ያድጋል፡፡ አጠገባችን ካሉ ሰዎች ጋር ባለንም ግንኙነት ታማኝነት ጥንቃቄና አትኩሮት ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ በቃላችንም ሆነ ተግባራችን አንዳችን በሌላችን ላይ እምነት የሚጣልብን ልንሆን ያስፈልገናል፡፡ ስለ እውነት የሚጠበቅብንን መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች ልንሆን ያስፈልገናል፡፡

ከሚቀጥለው ታሪክ ልንማር የምንችለው ትምህርት አለ፡፡ አንድ መምህር አንድን ልጅ እንዲህ ብላ ጠየቀችው “ለአንድ ብር ብለህ ውሸትን ትናገራለህ ?”

“አልናገርም መምህር” ሲል መለሰ ትንሹ ልጅ፡፡

“ለአምስት ብርስ ብለህ ውሸት ትናገራለህ?”

“አልዋሽም” አለ ልጁ፡፡

“ለአስር ብር ብለህ ውሸት ትናገራለህ”

“አልዋሽም” ነበር መልሱ፡፡

“ለአንድ ሺህ ብር ብለህስ ውሸት ትናገራለህ?

“ወይኔ” አለ በውስጡ “በአንድ ሺህ ብር ማድረግ የማልችለው ምን አለ?”

በማመንታት ላይ ሳለ ከኋላው የነበረ አንድ ሌላ ልጅ “አላደርገውም” አለ፡፡

“ለምን?” ጠየቀች መምህሯ፡፡

“ምክንያቱም ውሸት ይጣበቃል፤ አንድ ሺህ ብሩ ሲያልቅ፣ ከብሩ የሚገኘው ጥሩ ነገር ሁሉ ሲቆም ውሸቱ ግን እዛው እንደተጣበቀ ይቀራል”

እውነት ምቾት ቢነሳንም እንኳን ልንጠብቀው ፈቃደኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ከጊዜያዊ ሀፍረት ራሳችንን ለማዳን ብለን መዋሸት ሀቀኝነታችንን አሳልፈን በመስጠት የምንከፍለው ትልቅ ዋጋ ነው፡፡ እምነትን በማጉደል የሚገኝ ገንዘብ ለቆሸሸ ህሊና እና በዚህ አይነቱ ኃጢአት ላይ እግዚአብሔር ለሚያኖረው ዘላለማዊ ፍርድ የሚከፈል ትንሽ ዋጋ ነው፡፡ 

ከታች የተዘረዘሩት ዓይነት ክፉ ስራዎች እየሰራህ በእግዚአብሔር ብርሀን እመላለሳለሁ ትላለህን?

  • ወንድም እና እህቶችህን ይቅር አለማለት
  • ሰዎችን አሳዝነህ ጥፋትህን አለማረም
  • እውነትን ማጋነን
  • ቃልህን አለመጠበቅ
  • የእግዚአብሔርን መባ እና አስራት መስረቅ

ታማኝነት የባህርይ መመዘኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር ልባችንን ያውቃል፤ ከፊቱም የተሰወረ ምንም ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደሚያውቀን እና በውስጣችንም እንደሚሰማን ሆነን በእግዚአብሔር ፊት አንቀርብም፡፡ ታማኝነታችንን ወይም እውነተኛ ማንነታችንን  በሰዎች ፊት አንገልጠው ይሆናል፡፡ እውነተኛ ደስታ ያለው ሰው ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነና ትክክለኛ ማንነቱን የማይደብቅ ነው፡፡ ልባችንን ለእግዚአብሔር ግልጽ ስናደርግ እነዚህ ችግሮች መፍትሄን ያገኛሉ፡፡

አመለካከታችን እና መነሻ ሀሳባችን የታማኝነት ፈተናን ማለፍ አለባቸው፡፡ ይህንን ፈተና በእግዚአብሔር እና ሰዎች ፊት ለማለፍ ውስጣዊ የሆነ ለውጥ ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ውጫዊው ማንነታችን  የውስጣዊው ማንነታችን መገለጫ ነውና፡፡ ታማኝ ነህ? ታማኝነታችንን፤ እግዚአብሔር ይሻልዋል፣ ሌሎች ይጠብቁብናል፣ እኛም ተጠቃሚ እንሆንበታለን፡፡ የታማኝነት ህይወት ዋጋው እጅግ የከበረ ነው፡፡ “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር” ወደናል (ዕብራውያን 13፡18)፡፡ “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ” (ሮሜ 12፡17)፡፡  በተጨማሪ ዘሌዋውያን 19፡35-36 እና ምሳሌ 19፡5ን አንብብ፡፡

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ

አድምጥ! የሚጠራህ ማን ነው?

The listening lamb

የዮሐንስ ወንጌል 10፡ 1-18

አንድ ሰው ሲጠራህና የሚጠራህ ሰው ድምጽ ከየት አቅጣጫ እንደሚመጣ ለማወቅ ግራ ተጋብተህ ታውቅ ይሆን? ወይም ብዙ ጫጫታ መካከል ከመሆንህ የተነሳ የሚጠራህን ሰው ድምጽ ለመስማት ተቸግረህ ታውቅ ይሆን?

አድምጥ! አንድ ድምጽ እየጠራህ ነው፡፡ አዎ አንተን!

የተሟላ መልዕክት ክፍል አድምጥ! የሚጠራህ ማን ነው?

አንተ ማን ነህ? ስምህ ማን ነው? ከየት ነው የመጣኸው? የት ነው ምትኖረው? ወዴትስ እየተጓዝክ ነው?

የምትኖርበትን አካባቢ ስም ታውቃለህ፡፡ ድነገትም ከምትኖርበት አካባቢ ርቀህ ተጉዘህ አታውቅ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የምትኖርበት አካባቢ የአንድ አገር አካል፤ አገራት ደግሞ የአለም አካል እንደሆኑ ታውቃለህ;፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ

አለማችን ከተፈጠረች 6,000 ዓመታት ሆንዋታል፡፡ የተፈጠረችውም በእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምንና የመጀመሪያውን ሰው እንዴት እንደፈጠረ የተረከበት መጽሐፍ ቅዱስ የተባለ መጽሐፍ አለው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የፈጠረው በአምሳሉ ነው፡፡

ከዚያን ግዜ ጀምሮ ብዙ ልጆች ተወልደዋል፡፡ ብዙ ሰውችም ሞተዋል፡፡

አንተ የተወለድከው ከአባትና እናትህ ነው፡፡ ነገር ግን የሰራህ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ አንተን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ነገር የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉን ነገር እንዴት አድርጎ እንደ ሰራ እና አንተን እንዴት አድርጎ እንደፈጠረ አስበህ ታውቅ ይሆን? 

ወላጆችህ ስም አውጥተውልሀል፡፡ እግዚአብሔር ስምህን ያውቃል፡፡ በማንኛውም ቋንቋ ቢሆን እግዚአብሔር የእያንዳንዱን ሰው ስም ያውቃል፡፡ እርሱ ሁሉን አዋቂ ነው፡፡

እግዚአብሔር ፈጣሪያችን ስለሆን ስለ እኛ ሁሉን ያውቃል፡፡ እኛ የእርሱ ስለሆንን ይወደናል፡፡ እርሱ ከአባትና እናታችን ይልቅ አብልጦ የሚጠነቀቅልን በሰማይ የሚኖር አባታችን ነው፡፡

እግዚአብሔር

እግዚአብሔር የነበረ፣ ያለ እና ለዘላለም የሚኖር አምላክ ነው፡፡ ስለዚህም እስትንፋሱን በሰጠን ጊዜ እኛንም ለዘላለም እንድንኖር አድርጎናል፡፡ ነገር ግን ስጋችን ሟች ስለሆነ እርሱ ሳይሆን ለዘላለም የሚኖረው በውስጣችን የምትኖር ነብሳችን ነች ዘላለማዊ፡፡

እግዚአብሔርን ታውቀዋለህ? ድንገት “እግዚአብሔር ማን ነው? የትስ ነው የሚኖረው?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? አዎ! በርግጥም ማወቅ ትፈልጋለህ፡፡ ውስጥህ በርግጥም ማወቅ ይፈልጋል፡፡

እግዚአብሔርን አይተኸው አታውቅም፤ ታውቃለህ እንዴ? አላየኸውም ማለት እኮ ታዲያ እግዚአብሔር የለም ማለት አይደለም፡፡

አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ያለው፡፡ ከርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ ምክንያቱም እውነተኛ አምላክ በሰማይና በምድር የሚኖር አምላክ ነው፡፡ እርሱ በአንድ ጊዜ በሁሉም ቦታ ይገኛል፡፡

የእግዚአብሔር መኖሪያ የተዋበውና በላይ ያለው ሰማይ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ድምጹን በሚታዘዙ ሰዎች ልብም ውስጥ ይኖራል፡፡

“እግዚአብሔርን ለማወቅ እንዴት መማር እችላለሁ?” የሚለውን ጥያቄ ትጠይቅ ይሆን? እግዚአብሔር እንዴት ልናውቀው እንደምንችል ድንቅ መንገድን አዘጋጅቶልናል፡፡

እግዚአብሔር ማን እንደሆነ እና ምን እንደሚመስል ለሰዎች ሁሉ እንዲያሳይ አንድያ ልጁ የሆነውን ኢየሱስን ከሰማይ ልኮታል፡፡ አብና ወልድ አንድ ናቸው፡፡

የእግዚአብሔር ልጅ በተአምራት ህጻን ልጅ ሆኖ ተወለደ፤ ትልቅም ሰው ሆኖ አደገ፡፡ ኢየሱስ ካደገ በኋላ ለሶስት ዓመታት ስለአባቱ ፍቅር ለሰዎች አስተማረ፡፡ ጨምሮም እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነና ኃጢአትን እንደሚጸየፍ አስተማረ፡፡

ከዛም እግዚአብሔር ከኃጢአታችን የምንድንበትን መንገድ አዘጋጀልን፡፡ ልጁ ኢየሱስ በክፉዎች እጅ ወድቆ መስቀል ላይ እንዲሰቀል ፈቀደ፡፡ ኢየሱስ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሳ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ ሰጠ!

ኢየሱስ የዓለምን ሁሉ የኃጢአት ዋጋ ሊከፍል የቻለ መስዋዕት ነበር፡፡ አንተ ለሰራኸው ኃጢአት ሁሉ፤ ለትልቅ ለትንሹ፤ ለወንድ ለሴቱ ኃጢአት ሁሉ መስዋዕት የሆነው ኢየሱስ ነው፡፡

ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንደተሰቀለ ቀረን? በመቃብርስ ተቀብሮ ቀረ? በፍጹም፣ ከሶስት ቀን በኋላ በድል ተነስቶ ወደ ሰማይ አረገ፡፡ የዚህች ዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ የሰው ሁሉ ጻድቅ ፈራጅ ሆኖ ይገለጣል፡፡

የዮሐንስ ወንጌል ካለህ ምዕራፍ አስርን (10) አንብብ፡፡ ዮሐንስ ኢየሱስ ለህዝቡ ምን ያስተምራቸው እንደነበር ነው የጻፈው፡፡ ኢየሱስ ያን ጊዜ ለህዝቡ ያስተማረው ትምህር ዛሬ ለእኛም ትምህርት ነው፡፡ ኢየሱስ መልካም እረኛ እንደሆነ እና ነፍሱንም ስለ በጎቹ አሳልፎ እንደሰጠ ተናግርዋል፡፡ በጎቹ ደግሞ እኛ ነን፡፡ በጎቹ የሆኑት ድምጹን ያውቃሉ፡፡ እያንዳንዳቸውን በስም ይጠራቸዋል፤ እነሱም ሌላውን ከመከተል ይሸሻሉ፡፡

እንግዳው፤ ሌላኛው ድምጽ

እንግዳ የተባለው እና ልንሸሸው የሚገባው ማንን ነው? ኦ! ሌባውን ነው፡፡ እርሱ ስለ በጎቹ ምንም ደንታ የለውም፡፡ ውሸታም ስለሆነ አንዳች እውነት በእርሱ ዘንድ የለም፡፡ እርሱ ዲያብሎስ ነው፤ እርሱ ጠላታችን የሆነው ሰይጣን ነው፡፡

አስቀድሞ እርሱ የእግዚአብሔር ጠላት ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከእግዚአብሔር ጋር በሰማይ ይኖር የነበረ ቅዱስ መልአክ ነበር፡፡ ነገር ግን በትዕቢት እራሱን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ሊያደርግ ሞከረ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ተዋጋ፣ ብዙ መላእክትም ተባበሩት፡፡ እግዚአብሔር ኃያል ስለሆነ ድል በመንሳት ሰይጣንን ከነተከታዮቹ ከገነት አባረራቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ ሰይጣንን እግዚአብሔርን ይጠላዋል፡፡

ሰይጣን እግዚአብሔር አጠገብ መቅረብ ስለማይችል እግዚአብሔር በአምሳሉ በፈጠራቸው ሰዎች ላይ ተቆጣ፡፡ ሰይጣን ኃጢአተኛ ስለሆነ ሰው ሁሉ ኃጢአት እንዲሰራ ያባብላል፡፡ ኃጢአት ዳግመኛ ወደ ገነት ሊገባ ፈጽሞ አይችልም፡፡

እግዚአብሔር ለዲያብሎስ እና መላእክቱ ሁሉ የሰራው ሌላ ስፍራ አለ፡፡ ይህ ስፍራ ሲኦል ነው፡፡ ሲኦል እሳቱ የማይጠፋ  የስቃይ ቦታ ነው፡፡ ዲያብሎስ እና ተከታዮቹ ሁሉ ለዘላለም የሚቀጡበት ቦታ ነው፡፡ እኛም የሰይጣንን ድምጽ ለመስማት የምንመርጥ ከሆነ እግዚአብሔር ወደዚህ ቦታ ይልከናል፡፡

ሰይጣን ስለ ሲኦልም ሆን ስለ እግዚአብሔር እንድናስብ አይፈልግም፡፡ ስለ እግዚአብሔር እንድናስብ ስለማይፈልግ ስለ እግዚአብሔር የሆኑ ሀሳቦቻችንን ሁሉ በመስረቅ የእርሱን ድምጽ እንድንሰማ ሊያደርገን ይሞክራል፡፡

በውስጥህ ያን የተለየውን የእንግዳውን ድምጽ ሰምተህ ታውቃለህ?

ሰይጣን አንዳንዴ መልካም ነገር እንደሚሰጠን አድርጎ ያሳምነናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ “እኔ ከሌሎች የተሻልኩ ነኝ፤ እኔ ከማንም በላይ አስፈላጊ ሰው ነኝ፤ ቅድሚያ ለእኔ ነው የሚገባው፤ አለቀውም/አለቃትም፤ ለመብቴ መታገል አለብኝ፤ በቂ ስለማላገኝ ብሰርቅም ችግር የለውም፤ ሁሉ ስለሚዋሹ እኔም ብዋሽ ችግር የለውም፤ ምን እያሰብኩ እንደሆነ ማንም ስለማያውቅ ጸያፍ ሀሳቦችን ባስብ ምንም ችግር የለውም፤ በብልግና የተሞሉ ቃላት በጣም ስለሚያስቁ ምንም ችግር የለባቸውም” ብለን እንድናስብ ያደርገናል፡፡

በሌላ ጊዜ ደግሞ ተስፋ አስቆርጦን “የማልረባ ነኝ፤ በሕይወት መኖሬ ምንም ትርጉም የለውም” ብለን እንድናስብ ያደርጋል፡፡

እነዚህ ሁሉ የዲያብሎስ ድምጾች ናቸው፡፡ እርሱ ውሸታም ነው፤ እኛንም ውሸታሞች ሊያደርገን የሚጥረው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ሌባ ነው፤ እኛም እንድንሰርቅ የሚፈልገው ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ እኛም ሌሎችን የምንጠላ ሰዎች ሊያደርገን የሚጥረው ለዚህ ነው፡፡

ይህንን አይነቱን ድምጽ ስትሰማ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማሀል? ውስጥህን ደስ ያሰኝህ ይሆን? ኦ! በፍጹም ደስታ እንዳይሰማህ ያደርጋል፡፡ መደበቅ እንድትፈልግ ያደርግሀል፡፡ ሰይጣንም ልክ እንደዚህ ነው፤ ነገሮችን በጨለማ ተደብቆ ማድረግ ነው የሚወደው፡፡

ኢየሱስ፤ የእረኛው ድምጽ

መልካሙን እረኛ ኢየሱስን ታውቀዋለህን? የእርሱ በግ መሆን ትፈልጋለህን? ድምጹን ማወቅ ትፈልጋለህን?

አዎ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ ያንን ሌላኛውን ድምጽ መስማት ማቆም አለብህ፡፡

በጸጥታ ውስጥ ሆነህ ስታዳምጥ ኢየሱስ ዝግ ባለ ድምጽ ሕይወትህን አሳልፈህ እንድትሰጠው ጥሪን ሲያቀርብልህ ትሰማዋለህ፡፡ ኃጢአትህን ሁሉ ተናዘህ ንስሀ እንድትገባ ሲነግርህ ትሰማዋለህ፡፡    

አንዳንድ ጊዜ ተረጋግተህ ተቀምጠህ ሳለ “ችግሮቼን እና ሸክሞቼን ምን ላድርጋቸው? መልካም ሰው ብሆን እመኛለሁ፤ የማልታመምበት ወይም የማልራብበት ቦታ ብኖር ማናለ፤ ስሞት ምን እሆናለሁ?” የሚሉ ሀሳቦች አስበህ ሊሆን ይችላል፡፡

ድንገት ከእነዚህ የበለጡ ብዙ ሀሳቦች አስበህ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ድምጽ ኢየሱስ አንተን እየተጠራ ያለበት ድምጽ ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ምክንያቱን ሳታውቀው የሀዘን ስሜት ይሰማህ ይሆን? ወይም ሰው አብሮህ እያለ የብቸኝነት ስሜት ይሰማህ ይሆን? ይህ የሚሆንበት ምክንያት የፈጠረህና ሚወድህ እግዚአብሔር አብሮህ ስላልሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ የጠፉትን በጎቹን የሚፈልግ እረኛ ነው፡፡ ደጋግሞ እየጠራህ እና እየፈለገህ ነው!

የእረኛውን ድምጽ ስትሰማ መልስን ስጠው፡፡ ከኃጢአትህ ነጻ መውጣት እንደምትፈልግ ንገረው፡፡ የሚሰማህን ንገረው፤ እንዲያድንህም ጠይቀው፡፡ ጸሎት ማለት እንደዚህ ነው፡፡

ወደ ሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ጸልየህ ታውቅ ይሆን? አሁኑኑ ጸልይ፡፡ እርሱ ይሰማሀለ፤ ይረዳህማል፡፡ ዘወትር የምትናፍቀውን ሰላም ይሰጥሀል፡፡

የእርሱ በግ በመሆን ድምጹን ማወቅ ትፈልጋለህ? እርሱ ወዳጅህ ሊሆንህ እና ከኃጢአት ሸክምህ ሊያሳርፍህ ይፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ውስጥህ በደስታ ይሞላል፤ እንደ እርሱም አፍቃሪ እና ቸር ትሆናለህ፡፡ ፍራቻዎችህን ሁሉ ድል እንድትነሳ ይረዳሀል፡፡

ሌሎች ክርስቲያን በመሆንህ ቢያሾፉብህም አንተ ግን ኢየሱስ እንደሚጠነቀቅልህ ትረዳለህ፡፡ እንግዳው እየመጣ ቢፈትንህም ኢየሱስ እንድታሸንፈው እንደሚረዳህ ልታምነው ይገባል፡፡

በእረኛው የፍቅር እቅፍ ውስጥ ስታርፍ፣ እርሱ በመጨረሻ ድንቅ ወደ ሆነውና በደስታ ወደ ተሞላው ቤቱ ከእግዚአብሔር ጋር ለዘላለም እንድትኖር እንደሚወስድህ ትረዳለህ

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ