አርባ ስምንት ሰዓት በሲኦል

ጆን ሬይኖልድስ

ከማውቃቸው ታሪኮች በጣም ያስደነቀኝና እና ያነቃኝ በጄፈርሰን ግዛት በፈረስ ስርቆት ታዋቂ የነበረው የጆርጅ ሊኖክስ ታሪክ ነው፡፡ ይህ ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ተፈርዶበት በእስር ላይ ነበር፡፡ በመጀመሪያ የሴጅዊክ ግዛት በተመሳሳይ የፈረስ ስርቆት ወንጀል አስሮት ነበር፡፡

በእስር ላይ በነበረበት ወቅት እ.አ.አ በ 1987 እና 1988 የክረምት ወራት በከሰል ማዕድን ውስጥ ይሰራ ነበር፡፡ አንድ ቀን በስራ ላይ እያለ ይሰራ በነበረበት ቦታ ላይ አደጋ ሊከሰት እንደሆነ ተሰማው፡፡ ጉዳዩን ለቅርብ ኃላፊው አስረዳ፤ እሱም ይሰራ የነበረበትን ቦታ ከመረመረ በኋላ ምንም አስጊ ሁኔታ እንደሌለ ሲረዳ ሊኖክስን ወደ ስራው እንዲመለስ አዘዘው፡፡ እስረኛው ትእዛዙን ተቀብሎ ወደ ስራው ተመልሶ ለአንድ ሰዓት ያህል እንኳን ሳይቆይ ከላዩ የነበረው ድንጋይ ተደርምሶ ሙሉ ለሙሉ ቀበረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሁለት ሰዓታት ቆየ፡፡

የምሳ ሰዓት ላይ ስላልተገኘ የጠፋውን እስረኛ ፍለጋ ሲደረግ ከፍርስራሽ ክምር ስር ተገኘ፡፡ ሕይወቱ ያበቃ መሰለ፡፡ ካወጡት በኋላ የእስር ቤቱ ሐኪም በምርመራው መሞቱን አረጋገጠ፡፡ ሬሳውን ወደ ሆስፒታል ወስደው አጥበውና ገንዘው ለቀብር ስርዓት አዘጋጁት፡፡ የሬሳ ሳጥን ተዘጋጅቶ ወደ ሆስፒታል እንዲመጣ ተደረገ፡፡ ቄስ መጥቶም የመጨረሻ ጸሎተ-ፍትሐት አደረገ፡፡ ሁለት እስረኞች በድኑን በሬሳ ሳጥን ውስጥ እንዲያስገቡ በሆስፒታሉ ሹም ትዕዛዝ ተሰጣቸው፡፡ አንደኛው ራሱን ሌላንኛው እግሩን ይዘው በመሄድ ላይ እንዳሉ ራሱን ይዞ የነበረው እስረኛ ተደናቅፎ ሚዛኑን ሳተና ሬሳው ከእጁ አመለጠው፡፡ የሞተው ሰው ጭንቅላት ከመሬቱ ጋር ተጋጨ፤ በቦታው የነበሩ ሰዎች እስኪደነግጡና እስኪደነቁ ድረስ ከባድ የማቃሰት ድምፅ ተሰማ፡፡ ትንሽ ቆይቶ አይኖቹ ተከፈቱ ከዛም ሰውየው በሕይወት መኖሩን ያስረገጠ እንቅስቃሴን አደረገ፡፡ ሐኪሙ በፍጥነት እንዲመጣ ተጠርቶ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ በስፍራው ሲደርስ ሞተ ተብሎ የነበረው ሰው ውሃ እንዲሰጡት ጠይቆ እየጠጣ አገኘው፡፡

የሬሳ ሳጥኑ ወዲያውኑ እንዲወሰድ ተደረጎ በኋላ ላይ ሌላ እስረኛ ተቀበረበት፡፡ የመግነዝ ልብሱንም ወልቆ የእስረኛ ልብስ እንዲለብስ ተደረገ፡፡ በምርመራ አንድ እግሩ እንደተሰበረ እና እንደበለዘ ተረጋገጠ፡፡ በሆስፒታል ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ ወደ ስራው ተመለሰ፡፡

የዚህን ሰው እንግዳ የሆነ ልምምድ የሰማሁት በማዕድን ቁፋሮ አብሮት ይሰራ ከነበረ ሰው ነው፡፡ የታሪኩን እውነተኛነት ለማወቅ ጉጉት ስለነበረኝ ከሊኖክስ ጋር ለመተዋወቅና የሆነውን ከራሱ አንደበት ለመስማት እፈልግ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ይህን ለማድረግ አጋጣሚው አልተመቻቸም ነበር፤ በመጨረሻ ግን ተሳካ፡፡ ከማዕድን ስራ ከወጣሁ በኋላ በእስር ቤቱ ከነበሩ ቢሮዎች በአንዱ ውስጥ አመታዊ ሪፖርት በማዘጋጀት ስራ ላይ እንድሰራ ተመደብኩ፡፡ አንድ ቀን የዚህ ሰው ከሞት መነሳቱ እየተወራ እያለ በቢሮአችን በር በኩል አለፈ፤ ሰዎችም ማንነቱን ጠቆሙኝ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ወደምሰራበት ቦታ እንዲመጣ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ጠየኩት፡፡ እርሱም መጥቶ በደንብ ከተግባባን በኋላ አስደናቂ ታሪኩን ከራሱ አንደበት ለመስማት ቻልኩኝ፡፡ እድሜው ከሰላሳ የማያልፍ ወጣት ነው፡፡ አደገኛ ወንጀለኛ የነበረ፣ የተማረ እና በተፈጥሮው ብልሀተኛ የሆነ ሰው ነው፡፡

የተሟላ መልዕክት ክፍል አርባ ስምንት ሰዓት በሲኦል

የዚህ ሰው የሕይወቱ አስደናቂ ታሪክ የተከሰተው ሕይወቱ አልፎ በነበረበት ወቅት ነው፡፡ ታሪኩን ሲተርክልኝ እኔም እንደሚከተለው በማስታወሻዬ ላይ አሰፈርኩት፡፡

“የዚያን ቀን ጠዋት አንድ መጥፎ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ሲሰማኝ ነበር፡፡ ስጋቴ ስለባሰብኝ የማዕድን ስራ ኃላፊዬ ወደ ነበረው አቶ ግሬሰን በመሄድ የተሰማኝን ነግሬው እየቆፈርኩ የነበረበትን ክፍል መጥቶ እንዲመረምር ጠየኩት፡፡ መጥቶ ሁሉንም በጥንቃቄ ከፈተሸ በኋላ እየለጎምኩ እንደሆነ በማሰብ የሚያሰጋ ነገር እንደሌለ ነግሮኝ ወደ ስራዬ እንድመለስ አዘዘኝ፡፡ ወደ ስራዬ ተመልሼ ለአንድ ሰዓት ያህን እንደቆፈርኩ በድንገት ዙሪያዬ ሁሉ ጨለመ፡፡ ከዚያ ትልቅ የብረት በር  ወለል ብሎ ተከፍቶ በውስጡ እንዳለፍኩ ተሰማኝ፡፡ በቃ ሞቻለሁ፣ ያለሁትም በሌላ ዓለም ነው ብዬ አሰብኩ፡፡ የማየው ማንም ሰው ወይም የምሰማው ምንም አይነት ድምጽ አልነበረም፡፡ ያለ ምንም ምክንያት በበሩ አልፌ ሄድኩኝ፤ የተወሰነ ርቀት ተጉዤ ወደ ወንዝ ዳርቻ ደረስኩ፡፡ ጨለማ አልነበረም፤ ብርሃንም አልነበረም፡፡ በከዋክብት እንደ ደመቀ ምሽት ወገግ ያለ ብርሃን ነበር፡፡ በወንዙ ዳርቻ ላይ ብዙም ሳልቆይ አንድ ሰው ቆሜ ወደነበረበት ቦታ በጀልባ እየቀዘፈ መጣ፡፡

“ምንም አልተናገርኩም፡፡ ለትንሽ ጊዜ ትኩር ብሎ ተመለከተኝና ሊወስደኝ እንደመጣ አሳውቆኝ ወደ ማዶ ለመሻገር ጀልባ ውስጥ እንድገባ ነገረኝ፡፡ ታዘዝኩት፡፡ ምንም አልተነጋገርንም፡፡ ማን እንደሆነና የት እንዳለሁ ልጠይቀው ፈለግሁ ነገር ግን ምላሴ ከላንቃዬ ጋር የተጣበቀ መሰለኝ፡፡ አንድም ቃል መተንፈስ አልቻልኩም፡፡ በመጨረሻ ወደ ማዶ ወንዝ ዳር ደረስን፡፡ ከጀልባው ስወጣ ባለ ጀልባው ሰው ከእይታዬ ተሰወረ፡፡

“ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ ተጋብቼ ብቻዬን በቆምኩበት ቀረሁ፡፡ ወደ ፊት ስመለከት ወደ ጨለማ ሸለቆ ውስጥ የሚመሩ ሁለት መንገዶችን አየሁ፡፡ ከእነዚህ አንደኛው መንገድ ሰፊ እና ብዙዎች የተጓዙበትም የሚመስል ነበር፡፡ ሁለተኛው መንገድ ጠባብና ወደ ሌላ አቅጣጫ የሚያመራ ነበር፡፡ እኔም በደመነፍስ ብዙ የተኬደበት መንገድ ተከትዬ ሄድኩኝ፡፡ ብዙም ሳልኋዝ ጨለማው የበረታ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ አልፎ አልፎ በርቀት የመብራት ጭላንጭል ሲበራ ይታየኝ ስለነበር ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡

“መልኩ ምን እንደሚመስል ፈፅሞ ለመግለጽ ከሚከብድ ፍጡር ጋር በድንገት ተገናኘሁ፡፡ የዚህን ፍጡር አስቀያሚ ገጽታ ልገልጽልህ የምችለው በጥቂቱ ብቻ ነው፡፡ በተወሰነው ሰው ይመስላል ነገር ግን በአይኔ አይቼ ከማውቀው ሰው በጣም የገዘፈ ነበር፡፡ ቁመቱ ቢያንስ ሶስት ሜትር ይሆናል፡፡ በጀርባው ላይ ትላልቅ ክንፎች ነበሩት፡፡ የመልኩ ጥቁረት ልክ እቆፍር የነበረውን ከሰል ሲመስል ሙሉ ሰውነቱ ራቁቱን ነበር፡፡ በእጁ ጦር ይዟል፣ የእጀታው ቁመት አምስት ሜትር ያህል ይረዝም ነበር፡፡ አይኖቹ እንደ እሳት ኳስ ነበሩ፡፡ እንደ በረዶ ነጭ የነበሩ ጥርሶቹ ሶስት ሴንቲ ሜትር ያህል ይረዝሙ ነበር፡፡ አፍንጫው፣ አፍንጫ ከተባለ በጣም ትልቅ፣ ሰፊና ጠፍጣፋ ነበር፡፡ ፀጉሩ ከርዳዳ፣ ወፍራምና ረጅም በግዙፍ ትከሻውም ላይ ይቀመጥ ነበር፡፡ ድምጹ እንደሚያገሳ አንበሳ ነበር፡፡

“መጀመሪያ ያየሁት በመብራቱ ጭላንጭል ውስጥ ነበር፡፡ ባየሁት ጊዜ እንደ ቅጠል በፍርሀት እየተንቀጠቀጥኩ ባለሁበት ቆሜ ቀረሁ፡፡ እጁን ወደ ላይ ሲያነሳ ጦሩን ወርውሮ ሊወጋኝ መሰለኝ፡፡ በዚያ አስፈሪ ድምፁ በጉዞዬ ሊመራኝ እንደተላከ ነገሮኝ እንድከተለው አመለከተኝ፡፡ እኔም ተከተልኩት፡፡ ሌላ ምን ማድረግ እችል ነበር? የተወሰነ ርቀት ከሄድን በኋላ ትልቅ ተራራ በፊታችን ቆመ፡፡ አንድ ተራራ ለሁለት ተከፍሎ እንደኛው ክፋይ ከአጠገቡ የተወሰደ ይመስል በኛ ትይዩ ያለው ተራራ ወደ ላይ ቀጥ ብሎ የቆመ ነበር፡፡ በዚህ ቀጥ ባለ ተራራ ላይ “ይህ ሲኦል ነው” የሚል ጽሁፍ በግልጽ ይታየኝ ነበር፡፡ መሪዬ ቀጥ ብሎ ወደ ቆመው ግድግዳ ተጠግቶ በያዘው የጦር እጀታ ሶስት ጊዜ አንኳኳው፡፡ እጅግ ግዙፍ በር ወደ ኋላው ወለል ብሎ ተከፈተና አለፍንበት፡፡ ከዚያ በኋላ በተራራው ውስጥ መተላለፊያ በሚመስል መንገድ ውስጥ እንድሄድ ተመራሁ፡፡

“ለተወሰነ ጊዜ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ተጓዝን ፡፡ የመሪዬ ከባድ የእርምጃ ኮቴ ይሰማኝ ስለነበር ለመከተል አላዳገተኝም፡፡ በመንገዳችን ሁሉ ላይ ሰው ሊሞት ሲል የሚያሰማው ከባድ የጣር ድምጽ ይሰማኝ ነበር፡፡ እየቆየ የሚሰማው የጣር ድምጽ እየበረታ መጣ፡፡ ውሃ! ውሃ! ውሃ! የሚል የለቅሶ ድምጽ በግልጽ ይሰማኝ ነበር፡፡ ወደ ሌላ በር አልፈን ስንገባ ከሩቅ ውሃ! ውሃ! የሚል የአእላፋት የለቅሶ ድምጽ የሚሰማኝ መሰለኝ፡፡ በሚመራኝ ሰው ማንኳኳት አሁንም ሌላ ትልቅ በር ተከፈተ እና በተራራው ውስጥ ተጉዘን እንዳለፍን ተረዳሁ፡፡ በፊቴም ሰፊ ሜዳ ተንጣሎ ነበር፡፡

“መሪዬ ብቻዬን ትቶኝ ሌሎች የጠፉ ነፍሳትን ወደዚህ ቦታ መርቶ ለማምጣት ሄደ፡፡ በዚህ ገላጣ ሜዳ ላይ ለተወሰነ ጊዜ ቆየሁ፡፡ የመጀመሪያውን ፍጡር የሚመስል ሌላ ፍጡር ወደ እኔ መጣ፡፡ ይህንኛው ፍጡር ግን የያዘው ጦር ሳይሆን ትልቅ ሰይፍ ነበር፡፡ የመጣው የሚጠብቀኝ ፍርድ ምን እንደሆነ ሊያሳውቀኝ ነበር፡፡ ነፍሴን በፍርሀት ባስጨነቀ ድምጽ “ያለኸው በሲኦል ነው”፤ “ተስፋህ ሁሉ አክትሟል” አለኝ፡፡ በተራራው ውስጥ አልፈህ ወደዚህ ስትመጣ የተጠማ ምላሳቸውን ለማራስ ወሃ ውሃ እያሉ የሚጮኹትን የጠፉ ነፍሳትን የጣር እና የስቃይ ድምጽ ሰምተሀል፡፡ በመተላለፊያው ላይ ወደ እሳት ባህር የሚከፈት በር አለ፡፡ አንተም ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሚገቡበት ምንም የመውጣት ተስፋ ወደሌለበት ወደዚህ የስቃይ ቦታ መቼም ላትወጣ ትወርዳለህ፡፡ ወደዛ ከመላክህ በፊት ግን ከሚቀበሉት መከራ ይልቅ ይደሰቱበት የነበረውን ደስታ መመልከት እንዲችሉ ለጠፉ ነፍሳት ሁሉ እንደሚፈቀድላቸው ለአንተም በዚህ ሜዳ ላይ ለአጭር ጊዜ እንድትቆይ ተፈቅዶልሀል፡፡

“ይህን ተብዬ ብቻዬን ተተውኩኝ፡፡ ካሳለፍኩት ታላቅ ፍርሀት የተነሳ ይሁን አይሁን አላውቅም ፈዝዤ ቀረሁ፡፡ ተዝለፈለፍኩኝ፣ ድንዛዜ ሰውነቴን በሙሉ ተቆጣጠረኝ፡፡ ጉልበቴ ከዳኝ፡፡ ሰውነቴን መሸከም አቅቶኝ ወደ መሬት ወደቅኩ፡፡ እንቅልፍ ተጫጫነኝ፡፡ በሰመመን ሆኜ ህልም የማይ መሰለኝ፡፡ በርቀት ስመለከት በመጽሀፍ ቅዱስ ላይ እንደምናነብው አይነት ያማረች ከተማን አየሁ፡፡ ግንቦቿ በዕንቁዎች አሸብቀው አስደናቂ ውበት ነበራቸው፡፡ ባማሩ አበቦች የተሸፈነ የተንጣለለ ሜዳን በርቀት ተዘርግቶ ተመለከትኩ፡፡ እኔም የሕይወት ውሃ ወንዝን እና የብርጭቆ ባሕርን አየሁ፡፡ እጅግ ብዙ መላእክት ያማሩ መዝሙሮችን እየዘመሩ በከተማይቱ ደጆች ይገቡና ይወጡ ነበር፡፡ ከመካከላቸው በክፉ ባህሪዬ ልቧ በሀዘን ተሰብሮ የሞተችውን ውድ እናቴን አየኋት፡፡ ወደ እኔ እያየች ወደ እሷ እንድመጣ ምልክት የምትሰጠኝ መሰለኝ ነገር ግን መንቀሳቀስ አቃተኝ፡፡ ወደ ታች ስቦ የሚያስቀር ታላቅ ሸክም በላዬ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ ዝግ ያለ ንፋስ ሲነፍስ የአበቦቹን መልካም መአዛ ወደ እኔ ይዞ መጣ፡፡ ይህ ሲሆን የመላእክቱ ጣፋጭ የመዝሙር ዜማ ድምጽ ከመቼውም ይልቅ በግልጽ ይሰማኝ ነበርና “ምን አለበት፣ ከእነሱ እንደ አንዱ በሆንኩኝ” አልኩኝ፡፡

“ከዚህ ታላቅ የደስታ ጽዋ እየጠጣሁ ሳላ በድንገት ከአፌ ላይ ተነጠኩኝ፡፡ ከተኛሁበት ብድግ ተደረኩ፡፡ ከአስደሳቹ የህልም አለም በጨለማ መኖሪያ አጋሬ ተቀስቅሼ ነቃሁ፡፡ አሁን ወደ ዘላለማዊ መኖሪያዬ የምገባበት ሰዓት እንደሆነ ነገረኝ፡፡ እንድከተለው አመለከተኝ፡፡ የመጣሁበትን መንገድ ይዤ በመሄድ ወደ ጨለማው መመላለሻ ውስጥ ተመልሼ ከገባሁ በኋላ መሪዬን ለትንሽ ጊዜ ተከተልኩት፡፡ በመተላለፊያው በአንዱ ጎን ወደ ወደሚከፈት አንድ በር ደረስን በዚህ አልፈን ሄድን፡፡ በመጨረሻ በሌላ በር ስናልፍ ራሳችንን አገኘነው፡፡ ከዚያም የእሳት ባሕርን ተመለከትኩ፡፡

“ከፊት ለፊቴ አንስቶ አይኔ ማየት እስከሚችለው ርቀት ድረስ የእሳት ባሕር እና ዲን አየሁ፡፡ በማዕበል እንደሚናወጥ ባሕር ትልልቅ የእሳት ማዕበል እርስ በርሱ ይደራረብ እና ትልልቅ የእሳት ነበልባል እነደ ባሕር አውሎ ነፋስ ሞገድ እርስ በርሱ እየተጋጨ ወደ ሰማይ ላይ ይረጭ ነበር፡፡ በእሳቱ ማዕበል መከከል ሰዎች ወደ ላይ ብቅ ሲሉ አየሁ ነገር ግን ወድያው ወደ እሳት ባሕሩ ጥልቅ ክፍል ተመልሰው ይሰጥሙ ነበር፡፡ ከነበልባሉ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ብቅ ሲሉ ፃድቅ እግዚአብሔርን ሲሳደቡ መስማት አፀያፊ ነበር፡፡ ውሃ! ውሃ! የሚል የስቃይ ድምፃቸው አሳዛኝ ነበር፡፡ በዚህ ትልቅ የእሳት ባሕር ውስጥ የእነዚህ የጠፉ ነፍሳት የስቃይ ጩኸት ደጋግሞ ሲየስተጋባ ይሰማ ነበር፡፡

“ከጥቂት ጊዜ በፊት አልፌ ወደ ገባሁበት በር አይኖቼን ዘውር አድርጌ ስመለከት“ይህ ዘላለማዊ ፍርድህን የምትቀበልበት ስፍራ ነው” የሚል አሰቃቂ ጽሁፍን አነበብኩ፡፡ ወድያው ቆሜ የነበረበት መሬት ተሰንጥቆ ወደ እሳት ባሕሩ ውስጥ እየሰጠምሁ እንደሆነ ታወቀኝ፡፡ ለመግለጽ የማይቻል ኃይለኛ የውሃ ጥም ያዘኝ፡፡ ውሃ! እያልኩ መጣራት ስጀምር አይኖቼ ተከፍተው በእስር ቤቱ ሆስፒታል ውስጥ ራሴን አገኘሁት፡፡

“የእስር ቤቱ አዛዦች ይህንን ልምምዴን ከሰሙ አብዷል ብለው በማሰብ ወደ እብዶች ሆስፒታል ይከቱኛል ብዬ ስለፈራሁ ለማንም ተናግሬው አላውቅም፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ አልፌ አሁን በሕይወት ስላለሁ እና ልክ በመጽሀፍ ቅዱስ እንደሚናገረው አይነት መግስተ ሰማይ እንዳለ ሲኦልም እንዳለ በማወቅ አርፊያለሁ፡፡ ወደዚያ ሲኦል ስፍራ በጭራሽ ተመልሼ እንደማልሄድ እርግጠኛ ነኝ፡፡

“በሆስፒታል አይኖቼን ስከፍት በሕይወት እንዳለሁና እና ተመልሼ በምድር ላይ መሆኔን ሳውቅ ጊዜ ሳላጠፋ ልቤን ለጌታ ሰጠሁ፡፡ ካሁን በኋላ የቀረውን ህይወቴን ኖሬ የማልፈው አማኝ ሆኜ ነው፡፡ የሲኦል አሰቃቂ ገጽታ መቼም ከአዕምሮዬ ማይጠፋ ቢሆንም በመንግስተ ሰማይ ያየኋቸው ያማሩትንም ነገሮች አልረሳቸውም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ውዷን እናቴንም አገኛታለሁ፡፡ በዚያ በማረ ወንዝ ዳር መቀመጥ፣ በተንጣለለው ሜዳ፣ በሸለቆዎች እና አዕምሮ ሊገምተው ከሚችለው በላይ መአዛቸው በሚያውዱ አበባቦች የተሸፈኑት ኮረብቾች መካከል ከመላእክቱ ጋር መመላለስ፣ የዳኑ ነፍሳት የሚያዜሙትን ዜማ መስማት፣ ይሄ ሁሉ ከመታሰሬም በፊት እደሰትባቸው የነበሩ ብዙ አለማዊ ደስታዊችን እምቢ ብዬ በምድር ላይ በቅድስና ለምኖረው ሕይወት ልቀበለው ከሚገባኝ ዋጋ ያለፈ ነው፡፡ በውንብድና አጋሮቼ የነበሩትን ሁሉ ትቻቸዋለሁ፤ ከእስር ቤትም ስወጣ መልካም ከሆኑ ሰዎች ጋራ እወዳጃለሁ፡፡”

ይህንን ታሪክ ለአንባቢዎቻችን የምናደርሰው ከራሱ ከሊኖክስ እንደሰማነው ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህንን ታሪክ ተጠቅሞ ብዙ የጠፉ ነፍሳትን እንዲመልስ ፀሎታችን ነው፡፡

ሰዎች የሲኦልን እውነተኛነት እንዴት ሊጠራጠሩ ይችላሉ? ስለ ሲኦል መኖር የእግዚአብሔር ቃል መጽሀፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ አቶ ሊኖክስ በራዕዩ ያየውም ይህነንኑ ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ ቆም ብላችሁ አስተውሉ፡፡ እውነትን ተጋፈጡ፡፡ እያንዳንዱ የህይወት ድርጊትህ እየተመዘገበ ነው፡፡ እግዚአብሔር ኃጢአተኛ መሆንህን ተረድተህ ንስሀ ስትገባ ይቅር ይልሀል፡፡ የድነት ብቸኛው መንገድ ስለ ኃጢአትህ መስዋእት ሆኖ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም እንደፈሰሰልህ በማመን ከኃጢአት መንፃት ነው፡፡ ይቅርታን ከእግዚአብሔር ስትቀበል በልብህ ሰላም እና እረፍት ይሰጥሀል፡፡ ነፃ መሆን ትችላለህ፤ በምድራዊ ሕይወትህ እና ከአርባ ስምንት ሰዓታት በላይ ከሆነው የዘላለም የሲኦል ስቃይ አምልጠህ የመንግስተ ሰማይን ደስታ ማጣጣም ትችላለህ፡፡

ባለ ጠጋው ሰው እና አልዓዛር

(ሉቃስ 16፡19-31)

 ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር። አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር። ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ።በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ።እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ።አብርሃም ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ።ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ።እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ።አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው። እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ።ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።

ተጨማሪ የሚነበቡ ጥቅሶች፡- ራዕይ 21፡7-8 ፣ ራዕይ 20፡10፣12፣13 ፣ 2ኛ ጴጥሮስ 3፡10-12

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ