በየትኛው መንገድ ልጓዝ?

ህይወት እንደ ጉዞ መሆኑን ታውቅ ነበር? የህይወት ጉዞ ወደ ሁለት ቦታ የሚያደርሱ ሁለት ጎዳናዎች አሉት፡፡ በየትኛው መንገድ ላይ ለመጓዝ መምረጥና መወሰን የአንተ ነው፡፡

በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ልጅ ሲወለድ የህይወትን ጉዞ ይጀምራል፡፡ በሰማይ የሚኖር አምላክ ለታዳጊ ልጆች ልዩ መንገድን ያደርጋል፡፡ ይሄ መንገድ የየዋህነት፣ እራስን ወደ ማወቅ የሚያመጣ መንገድ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ላይ እናትና አባት ለልጆች ስለ ህይወት በማስተማር መሪዎች ናቸው፡፡

በልጅነት በዚህ መንገድ ላይ ለተወሰነ ጊዜ በንፅህና ትጓዛለህ፤ ነገርግን በኋላ ላይ ወደ መንታ መንገድ ትደርሳለህ፡፡ የልጅነት እና የአለማወቅ ጎዳና ያበቃል፤ ከዚያም ወደ የተለያዩ ቦታ የሚወስዱ ሁለት መንገዶች ፊት ትመጣለህ፡፡ እስከ እዚህ ጊዜ ድረስ ወላጆችህ መሪዎችህና በዋናነት ውሳኔዎችህን ሲወስኑልህ ቆይተዋል፡፡ ወደዚህ መስቀለኛ መንገድ ከመጣህ በኋላ ውሳኔው የአንተ ሆንዋል፡፡ የትኛውን መንገድ ልምረጥ? ይህ ውሳኔ እጅግ ዋና፣ ከሁሉ በላይ የህይወትህ ትልቅ ውሳኔ ነው፡፡ ይህ ውሳኔ እጅግ ዋና የሆነበት ምክኒያት አንደኛው መንገድ መልካም፣ ንፁህ ህይወት፣ በደስታ የተሞላ ወደ መንግስተ ሰማይ የሚመራ መንገድ ነው፡፡ ሌላንኛው  የሀጢአተኝነት እና የክፋት መንገድ፣ በሀዘን የተሞላ፣ ወደ ገሀነም የሚመራ ነው፡፡

ወደ እነዚህ መንገዶች መድረሴን አንዴት ማወቅ እችላለሁ? የተቀመጠ ህግ ወይም እድሜ የለም፡፡አንዳንድ በልጅነት ጎዳና ላይ ያሉ ልጆች በህይወታቸው ከሌሎች ቀድመው ወደ መስቀለኛው መንገድ ይደርሳሉ፡፡ ምናልባትም መስቀለኛ መንገዶቹ ሰውየው ወንጌልን እስከሰማበት ጊዜ ድረስ ወይም የተሸለ መንገድ እንዳለ እስከሚረዳበት ጊዜ ድረስ አይደረስባቸውም ይሆናል፡፡ ምናልባትም ለብዙዎች ወንጌል በሰሙበት ሰእት የልባቸው መምታትና የመክበድ ስሜት ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክል ስለ ሆነው እና ስላልሆነው ግንዛቤ ወይም ጌታን ለመከተል መሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ የመስቀለኛ መንገዶች ምልክት ናቸው፡፡ በሁሉም ሁኔታ እግዚአብሔር የፍቅር አምላክ ስለሆነ የሁለቱን መንገዶች ምንነት ያሳውቀናል፡፡ ጠባቡ መንገድ በየትኛውም አገር እና ባህል ውስጥ ለሚኖር ፍጹም እንደሆነ ይገልጥለታል፡፡

በመስቀለኛው መንገድ ፊት ቆመህ ምን ትመለከታለህ?

ሁለቱን መንገዶች በደንብ አስተውላቸው፡፡ መጀመሪያ ላይ ሁለቱም መንገዶች አትኩሮትን የሚስቡ ናቸው፡፡ ቀረብ ብለህ ስታስተውል አንደኛው መንገድ ሰፊ ደግሞም ለመጓዝ ምቹና ቀላል እንደሆነ ታያለህ፡፡ ሌላንኛው መንገድ ጠባብ በተላያዩ ቦታዎች ኮሮኮንችና ዳገታማ የሆነ ነው፡፡ ሰፊው መንገድ ብዙ ብዙ ሰዎች የሚጓዙበት ነው፡፡ ጠባቡ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ይዟል፡፡ ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

ግራ ተጋብተሃል እና የትኛውን መንገድ መምረጥ እንዳለብህ እርግጠኛ አይደለህም? ብዙ ተጓዥ ወዳለው ሰፊ መንገድ ጠጋ ስትል የመንገዱ መሪና ጌታ ከእርሱ ጋር እንድትጓዝ ሲጠይቅህ ትሰማለህ፡፡ በመጀመሪያ መንገዱ የጠባቡን መንገድ አይነት ይመስላል፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ጉዞ የሚጀምሩ መልካም ሀሳብ አላቸው፡፡ ብዙዎች ለጊዜው በዚህ መንገድ ላይ ካሉ ወጥመዶች መቆጠብ ይችላሉ፡፡ የመሪው ታሪክ አርቴፊሻል ቢሆንም ለጆሮ ደስ የሚልና የሚያባብል ነው፡፡ በጉዞው መሀል ብዙ ጓደኞችን ያቀርብልሀል፤ ማንም ግን ከልቡ ደስተኛ አይመስልም፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ያሉ መዝናኛዎች ገደብ የላቸውም፡፡ መጠጣት፣ ማጨስ፣ መጨፈር፣ፓርቲዎች እና ሌሎች ብዙ መዝናኛዎች አሉት፡፡ ግብረገብነትና ስነ ስርአት ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ውሸት፣ ስርቆት እና ማታለል የተለመዱ ተግባሮች ናቸው፡፡ በዚህ መንገድ ላይ የፈለግከውን አይነት የህይወት ስታይል ትመርጣለህ፡፡ እንዳሰኘህ መሆን ትችላለህ፡፡ ነፃነት ይሉታል፡፡ ይህ መንገድ ብዙ ይዞህ ይጓዛል እናም ምቹ ስለሚመስል እያባከንክ ያለኸውን ጊዜህን አታስተውለም፡፡ በዚህ ጎዳና ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ለብዙ የተወሳሰቡ ነገሮች ባሮች ከመሆናቸው የተነሳ መውጫ መንገድ አይታያቸውም፡፡ ተስፋ መቁረጥ፣ ሀሽሽ (ሱስ)፣ ግድያ እና ራስን ማጥፋት ውጤቶቹ ናቸው፡፡

የተሟላ መልዕክት ክፍል በየትኛው መንገድ ልጓዝ?

በህይወትህ የምትፈልገው ይህን ነው? መጓዝ የምትፈልገው በዚህ ጎዳና ላይ ነው? የዚህ መንገድ መሪ በመንገዱ የመጓዝ የመጨረሻ እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ምንም አመማሳወቁን  አስተውለሀል? አያደርገውም፤ እራሱን አይክድም፡፡ የበግ ልብስ የለበሰ ተኩላ ሰይጣን ነው፡፡ በሰፊው መንገድ ላይ ለመጓዝ የሚከፍለው ብድራት የማይጠፋ የእሳት ባህር ሲኦል ነው፡፡ ይህ ቦታ የተዘጋጀው ለዳቢሎስና ለጭፍሮቹ ነበር፡፡ በዚያ ለዘለአለም ልቅሶ፣ ዋይታ እና ጥርስ ሟፏጨት ይሆናል፡፡ አንተስ? ከእርሱ ጋር ተጉዘህ የሲኦልን ብድራት መቀበል ትፈልጋለህ?

ጠባቡን መንገድ ቀረብ ብለህ ተመልከተው፡፡

ይህ መንገድ ከሰፊው መንገድ በእጅጉ ይለያል፡፡ ዳገታማ መንገድ እና ኮረብታና ሸለቆዎች በተለያዩ ቦታዎች ያሉት ነው፡፡ ፀሀይና ሙቀት አለበት ነገርግን መንገዱን ይዘህ ከሄድክ ጥምን ወደሚያረካ ምንጭ ትደርሳለህ፡፡ በዚህ አረፍት ታደርጋለህ፣ ውሀን ትጠጣለህ፡፡ ከጅረቶቹም መሚፈሰው ውሀ በመንገድ የደከሙ እግሮችህን ታርሳለህ፡፡ ታድሰህ መንገድህን ትቀጥላለህ፡፡ የሚወጡ ተራሮችም አሉት፤ አንዳንዴም መንገዱ የደበዘዘ ሊመስል ይችላል፡፡ በመንገድህ ስትቀጥል ወደ ተራራ ጫፍ ትደርሳለህ ከዚያም ለምለምና አረንጓዴ ወደ ሆነ ሸለቆ ይመራሀል፡፡ በጠባቡ መንገድ ላይ ያሉ ወዳጆችህ ሁሉ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ወንድምና እህት ይሆኑሀል፡፡ ይወዱሀል፣ ይጠነቀቁልሀል፡፡ በመንገድህ ተደናቅፈህ ስትወድቅ ተመልሰህ በእግሮችህ እንድትቆም ያግዙሀል፡፡ የሚረዱህና ደጎች ናቸው፡፡ ከሁሉም የሚበልጥ መሪና የግል ወዳጅ ግን አለህ፡፡ እሱ ጌታ ነው፤ መልካሙ እረኛ (መዝሙር 23)፡፡ በጣም ስለሚወድህ ከጎንህ በመሆን በጠባቡ መንገድ አብሮህ ይጓዛል፡፡ መንገድህ የጨለመና ከባድ ሲሆንብህ እጅህን ይዞ በግለጽ ማየት እስክትችል ይመራሀል፡፡ ተጓዡ ሲደክመው እና መንገዱም አደገኛ ሲሆን  እረኛው በክንዶቹ ይሸከምሀል፡፡ ከጊዜ በኋላ በእግርህ መንገዱን ለመቀጠል ከድካምህ ትበረታለህ፡፡ በጠባቡ መንገድ የምትጓዘው እንዲህ ይሆናል፡፡

 እነዚህ ጠባብና ሰፊ የሆኑ ሁለት መንገዶች  በህይወት ጉዞ መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃሉ፡፡ በመንገዶቹ መጨረሻ ሞትን እንጋፈጣለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሞት ማለት  ወንዝ መሻገር ነው ይባላል፡፡ ሁሉም ሰው ይሻገረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ፍርድ ይሆናል፤ እግዚአብሔር አራሱ ስለ ተጓዝንበት መንገድ ፍርድ ይሰጣል (እብራውያን 9፡27)፡፡

እነዚያ በሰፊው መንገድ ላይ ከሰይጣን ጋር እየመራቸው ሲጓዙ የነበሩት የመሻገሪያ ወንዙን አስፈሪ ሆኖ ያገኙታል፡፡ ለምን? ወንዙን አብረውት የሚሻገሩት የላቸውም፡፡ ወዳጆቻቸው ሞትን የሚፈሩ ናቸው፡፡ ብቻቸውን መሻገር ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚያም በገሀነም እውነታ ፊት ይነቃሉ፤ ለጥልቀቱ መጨረሻ በሌለው በማይጠፋ የእሳት ባህር ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡

የበጠባቡ መንገድ ተጓዥ ከሆንክ ግን የመሻገርያ ወንዙን ትናፍቃለህ፤ ከወንዙ ማዶ አክሊልህ ይጠብቅሃል፡፡ ጊዜው ውብ ነው፤ ሰላማዊ ጊዜ፤ መልካሙ እረኛ በሞት ወንዝ መርቶ ያሻግርሃል፡፡ ከዚያ በሰማያዊ መኖሪያህ፤ በዚያ ጎዳናዎቹ በወርቅ የተሰሩ፣ ቃላት ሊገልጸው የማይችል የመላእክት ዝማሬ ባለበት ትሆናለህ፡፡ ከዚህ በኋላ የምትወጣቸው ዳገቶች አይኖሩም፣ የምትሻገራቸው ሸለቆዎችም የሉም፤ ሰላም፣ ጸጥታ እና ደስታ ከዘለአለም እስከ ዘለአለም ብቻ ይሆናል፡፡ መሪ ጌታህ ደግሞ ከአንተ ጋር ይሆናል፡፡ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና” (ራዕይ 21፡4)፡፡

የትኛውን መንገድ ትመርጣለህ? ምላሽህ ምንድን ነው? የምትመርጠው ምርጫ በጣም ወሳኝ እንደሆነ አስታውስ፡፡ መንግስተ ሰማይ ወይስ የገሀነም እሳት ነው፡፡ ጠባቡን መንገድ ምረጥ፣ ጌታም እንዲረዳህ ጠይቀው፡፡ “በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” (ማቴዎስ 7፡13-14)፡፡

ለተጨማሪ መረጃ ያግኙን

በረሪ የውንጌል ጽሑፎችን (ትራክቶችን) ለማዘዝ